ሀገሬ ቲቪ

የቦክሱ ዓለም ንጉስ ልደት

ዓለም ስለሱ አንስቶ አይተግብም ፤ የነጭ እጁ ተአምረኛ፣ የሪንግ ውስጥ ንጉስ።

የ56 ሪከርዶች ባለቤት፣ ለሰውነት የቆመ ቆራጥ፤ ነጮች በነገሱበት ዓለም ውስጥ የተገኘ የጥቁሮች መመኪያም ጭምር።

የ20 ኛው ክፈለ ዘመን የቦክሱ ዓለም ጥበበኛ መሀመድ አሊ፤ በቀደመ ስሙ ካሲየስ ማርሴለስ ክሌይ ጁኒየር። የካሲየስ ማርሴሉስ ክሌይ ሲር ታላቅ ልጅ የተወለደው ሉዊስቪል፣ ኬንታኪ ነው።

አሊ ነጮች እን ጥቁሮች በአንድ ለመታየት እንኳን በማያልሙበት በዚያን ግዜ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ አልፏል። እናቱ ከአሜሪካው ሲቪል ጦርነት በኋላ ወደ አሜሪካ የፈለሱ ቤተሰብ ልጅ ናት፤ አባቱ ደግሞ በቀኝ ግዛቱ ዘመን ከማዳጋስካር ከመጡ የባሪያ ቤተሰቦች የተገኘ ነው።

የአሊ አባት ለጥቁሮች እኩልነት አብዝቶ የሚታገል ነበር። የቆዳ ቀለሙ ከነጮች መለየቱ አየአሊን ልጅነት ፈትኖታል። አሊ በ13 ዓመቱ ነጭ ሴትን አብሳጨህ በሚል በሚሲሲሲ በነጮች መዳፍ ክፉኛ ተደብድቦ፣ በግፍ የተገደለው የሚሲሲፒው ታዳጊ የ14 ዓመቱ ኤሜት ሉዊስ ቲል ነገር እስከ እድሜው ፍፃሜ ድረስ ያንገበግበው እንደነበር ተናግሯል።

ያኔ ገና በ12 ዓመት እድሜው የተሰረቀበትን ሳይክል ለማመልከት ወደ ፖሊስ ኦፊሰሩ ጆ ማርቲን ሄደ። ሳይክሉ እንደጠፋበት እና ሌባውን ቢያገኝው ሊመታው እንደሚፈልግ ነገረው፤ የቦክስ አሰልታኙ እና የፖሊስ ኦፊሰሩ ማርቲን አስቀድሞ እንዴት ቦክስ መሰንዘር እንዳለብት መማር እንዳለበት ነገረው።

አሊ የኦፊሰሩን ምክር ከቁብም አልቆጠረውም ወደቤቱ ተመልሶ ሄደ። በማግስቱ የጀማሪዎች የቦክስ ፍልሚያ ውድድርን በቴሌቪዥን መስኮት ተመለከተ ልቡ ወደ ቦክስ ስፖርት ሸፈተ።

የፕሮፌሽናል የቢክስ ህይወቱ ፍሬድ እስቶነር ከተባለ የቦክስ ስፖርት አሰኝ ጋር አንድ ብሎ ጀመረ።አሊ ስለ እስቶነር ሲናገር እሱ የምርም አሰልጣኝ ነው ይለዋል።

አሊ በጀማሪ የቦክስ የቦክስ ስፖርት ህይወቱ የተሸነፈው 5 ውድድሮችን ብቻ ነው፤ 100 ዎቹን ባለክብር ሆኖባቸዋል።

አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ድል ባረገባት ሮም 1952 ኦሎምፒክ ሌላኛው ጥቁር ሰው በጥቋቁር እጆቹ የወርቅ ሜዳሊያን አጥልቆባታል።

ይህ የጥቁሮች ሌላኛው ኩራት የጥቁሮች መብት ተሟጋች ማልኮም ኤክስን ተከትሎ የኔሽን ኦፍ ኢስላምን ተቀላቀለ። በየካቲት 27 1956 ዓ.ም. ስሙም በይፋ መሀመድ አሊ ተብሎ ተቀየረ።

ከማይረሱ የቦክሱ ዓለም ክስተቶች አንዱም በአፍሪካ ምድር ሆነ ራምብ ኢን ዘጃንግል የአናብስቱ ፍልሚያ በአፍሪካ ምድር ዛሬ ለሁለት በተከፈለችው በቀድሞዋ ዛየር በአሁኗ ኮንጎ ኪንሻሳ እንዲህ ሆነ።

ጥቅምት 20 1967 ዓ.ም. የቦክሱ ንጉስ መሀመድ አሊ ከግዙፉ ጆርጅ ፎርማን ጋር ተፋጠጡ። አዘጋጁ ደግሞ ስፖርትን አብዝተው የሚወዲት አበገነን ናቸው በሚል ስማቸው የሚብጠለጠለው ማቡቱ ሲሴኮ ናቸው።

በዚያ የ20ኛው ክፍለ ዘመን የማይረሳ የቦክስ ውድድር ተደረገ። በግዜ እድሜው 32 የነበረው አሊ ወጣቱን 24 ዓመት አስፈሪውን ፎርማንን በ8ተኛው ዙር ከመሬት ላይ ዘረረው። ይህ ከመሀመድ አሊ የቦክ ህይወት ታሪክ ውስጥ የማይዘነጋ ሆኖም ተመዘገበ።

የቦክስ ዓለም የምን ግዜም ምርጥ ቦክሰኛ ለ32 ዓመታት በየፓርኪንሰን ህመም ሲሰቃይ ቆይቶ በ74 ዓመቱ በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም ይህችን ዓለም ተሰናበተ።

ይህ ተዓምረኛ የቦክስ ስፖርቱ ንጉስ፤ ፈጣኑ ቦክሰኛ በብዙ የሚዘመርለት፤ የ20ኛው ክፍለዘመን ስጦታ፣ በሪንግ ውስጥ በቆየባቸው ዓመታት ስሙን በወርቅ ቀለም ማፃፍ የቻለ ኮከብ በጥር 9 1934 ዓ.ም ልክ በዛሬው ቀን ይህችን ዓለም ተቀላቀለ።

የዛሬ 81 ዓመት የቦክሱ ንጉስ መሀመድ አሊ ተወለደ።

በሳምሶን ገድሉ
2023-01-17