ሀገሬ ቲቪ

የ ስካውት አመሰራረት

ታዳጊዎች መልካም ነገርን፣ ሰብአዊነትን፣ በጎነትንና ሌሎች መልካም እሴቶችን እንዲያድጉ ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ የሚሰራ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚንቀሳቀስ ማህበር ነው ። ስካውት ።

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ ታዳጊዎች ነጋቸው እንዲያምር ከስር ከመሰረቱ የሚሰራው ስካውት የተሰኘው ማህበር መች ተመሰረተ ብለን መዛግብቶችን ስናገላብጥ በዛሬዋ ዕለት ጥር 16 ቀን 1908 በመሆኑ የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ልናደርገው ወደድን።

ስካውትን መስርተው ለዓለም ያስተዋወቁት ሎርድ ቤደን ፓዎል የተባሉ የ ወቅቱ የታላቋ ብሪታንያ ወታደራዊ አዛዥ ናቸው። ወታደራዊ አዛዡ ሰፊ ጊዜያቸውን ከወጣቶች ጋር በሚያሳልፉበት ወቅት በታዳጊዎች ውስጥ ሀገር መገንባት የሚችል ሀይል እንዳለ ይረዳሉ ።

ታዳጊዎች ችሎታቸውን አውጥተው እንዲያሳዩ ፤ በስነምግባር እንዲታነጹና ግዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙም ስልጠናዎች ሊሰጣቸው እንደሚገባ በማሰብ ስካውቲን ፎር ቦይስ የተሰኘ መጽሀፍ በመጻፍ ለገበያ ያቀርባሉ።

ፓዎል በመጽሀፋቸው ታዳጊ ወንዶችን መሰረት ያደረጉ አስተማሪ ታሪኮችን የከተቡ ሲሆን ከጥቂት ወራት በኋላም ከወጣቶቹ ጋር በአካል እንዲገኛኙ የሚያስችላቸውን የስካውት እንቅስቃሴ በዛሬዋ ቀን በ1908 አቋቋሙ ።

ታዳጊዎች ላይ የሚሰራው እንቅስቃሴ በ እንግሊዝ ሀገር ቢጀመርም ቀጣይ ፊታቸውን ወደ አፍሪካ በማዞር የአፍሪካ ወጣት ሀይሎችን በዚህ ዘመቻ ማነቃቃት ጀመሩ።

በኬኒያ ፤ ደቡብ አፍሪካ ፤ እንዲሁም በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች በስነምግባር የታነጹ ወጣት ሀይሎችን ያፈራው ስካውት በ1911 ዓ.ም በኋይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በልኡል መኮንን የበላይ ጠባቂነት በኢትዮጵያ ተቋቋመ።

በወቅቱ ያሉ ታዳጊዎችም ከሚወስዱት የውትድርና ስልጠና ጎን ለጎን ለፈጣሪ ታዛዥ እንዲሆኑ እንዲሁም በስነምግባር እንዲታነጹ ስካውት የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠት ጀመረ።

ስካውት ጅማሮውን ወጣት ወንዶች ላይ ያደረገ ቢሆንም በጊዜ ሂደት ሴቶችንም በመቀላቀል ራሳቸውን ፤ ቤተሰባቸውን እንዲሁም ፤ ሀገራቸውን የሚጥቅሙ ታዳጊዎችን ለረጅም አመታት ሲያፈራ ቆይቷል።

በአሁኑ ጊዜም የኢትዮጵያ ስካውቲንግ ማህበር በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ታዳጊዎችን በማሰልጥን ነጋቸውን ለማሳመር እየሰራ ይገኛል ።

በዮሴፍ ከበደ
2023-01-24