የአዲስ አበባ ቴአትርና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ፊልሞችን ማምረት ሊጀምር ነው
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያዎቹን ፊልሞች ከሰሩ ሀገራት አንዷ ስትሆን፣ በዘመነ ደርግ የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን ተቋቁሞ ፊልሞች ይመረቱ ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ውጥረት እና ተስማሚ የሃሳብ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ተቋሙ መክሰሙ የብዙዎች ቁጭት ነበር።
ዜና ክፍል · · 2 ደቂቃ ንባብ · 4

ሲኒማ የሀገርን ማንነት እና እሴቶች ከሚያስተዋውቁ ቁልፍ የኪነ-ጥበብ ስራዎች አንዱ ነው። በአንዳንድ ሀገራት ደግሞ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በመሆን ለኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ ለዚህም የአሜሪካው ሆሊዉድ ዋነኛ ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያዎቹን ፊልሞች ከሰሩ ሀገራት አንዷ ስትሆን፣ በዘመነ ደርግ የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን ተቋቁሞ ፊልሞች ይመረቱ ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ውጥረት እና ተስማሚ የሃሳብ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ተቋሙ መክሰሙ የብዙዎች ቁጭት ነበር።
የሲኒማ ዘርፉ በአብዛኛው በግለሰቦች ጥረት ብቻ የተገደበ፣ በበርካታ ችግሮች የተተበተበና ከአለም የሲኒማ ይትባህል ጋር የተራራቀ በመሆኑ የሀገራችን የሲኒማ እድገት የፊልም ስራን ከአፍሪካ ቀድማ እንደጀመረች ሀገር ፈጣን ለውጥ ማሳየት አልቻለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የፊልም ኢንዱስትሪውን ሊያግዙ እና አቅጣጫ ሊያስይዙ የሚችሉ አበረታች ዜናዎች ከአዲስ አበባ ቲያትርና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ተሰምቷል።
የአስተዳደሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ማንያዘዋል ጌታቸው ከሀገሬ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ‘’የአዲስ አበባ ቲያትርና ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር በአዋጅ ከተቋቋመ ሁለት ዓመታት ገደማ ያስቆጠረ ሲሆን አሁን ደግሞ ተቋማቱ በጋራ በመተባበር ከኪነ-ጥበብ ትርዒቶች አቅርቦት ባለፈ በቀጥታ ወደ ፊልም ምርት የሚሸጋገሩበት አሰራር ተዘርግቷል’’ ብለዋል።
በዚህም መሰረት ሲኒማ ቤቶቹ ፊልሞችን ከማሳየት ባለፈ ራሳቸው አምራች የሚሆኑበት ሁኔታ ይመቻቻል። ይህንን ስራ ለማሳካትም በከፊል የግል አጋርነትን መሰረት ባደረገ አደረጃጀት እንዲዋቀሩ ተደርጓል።
በዚህ እቅድ መሰረት መንግስት የበጀት ድጎማ የሚያደርግ ሲሆን፣ ሲኒማ ቤቶቹ ደግሞ የስራ ፈጠራ እና የገቢ ማመንጨት አቅማቸውን በማሳደግ ራሳቸውን የቻሉ የፊልም አምራቾች ይሆናሉ ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም እንደ “ዘመን ሲኒማ” ያሉ በሀገራችን የወጣቶች እና የህጻናት ሲኒማን ያካተተ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የያዘ ሲኒማ በብሄራዊ ቴአትር ፊትለፊት በቅርቡ የገነባ ሲሆን ፍላሚንጎ የተገነባው ዘመናዊው የህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤትም የዚህ አጠቃላይ እርምጃ አካል መሆኑ ተገልጿል።
