ወደ ዋናው ይዘት ዝለል

የኢትዮጵያንና የጃፓንን የባህል ትስስር ለማጠናከር ያለመው የ2026 የጃፓን ፊልም ፌስቲቫል ተከፈተ

በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል ያለውን የሕዝብ ለሕዝብና የባህል ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመው የ2026 የጃፓን ፊልም ፌስቲቫል በይፋ ተከፍቷል።

ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 1

በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ያዘጋጀውን ፌስቲቫል ላይ የኤምባሲው ምክትል አምባሳደር ሺገሩ ሃማኖ፣ ኤምባሲው ኢትዮጵያንና ጃፓንን ለማስተሳሰር ዘርፈ ብዙ ተልዕኮዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የጃፓንን ባህል በኢትዮጵያ ማስተዋወቅና የሕዝቡን ስለ ጃፓን ያለ ዕውቀት ማሳደግ የዚሁ ጥረት ዋነኛ አካል መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም ፊልሙ በዘመናዊው የጃፓን ባህል ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መስክ በመሆኑ ሁለቱን ሕዝቦች በሃሳብና በባህል ለማቀራረብ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።

የጃፓን የሲኒማ ታሪክና ልዩ ባህሪ በተዳሰሰበት መድረክ የፊልም ጥበብ ከ130 ዓመታት በፊት ማለትም እ.ኤ.አ በ1896 በምዕራባውያን ቴክኖሎጂ አማካኝነት ወደ ጃፓን መግባቱን ያስታወሱት ምክትል አምባሳደር ሺገሩ ሃማኖ፣ ጃፓናውያን ቴክኖሎጂውን ከተቀበሉ በኋላ በራሳቸው ዜጎችና ለራሳቸው ሕዝብ የሚሆኑ ፊልሞችን በፍጥነት መሥራት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በተለይም የጃፓን ሲኒማ እንደ ካቡኪ ፣ ኖህ እና ቡንራኩ የአሻንጉሊት ትያትር ባሉ የሀገሪቱ ጥንታዊና ባህላዊ የትወና ጥበባት በመቃኘቱ ከምዕራባውያን ሲኒማ የተለየ የራሱ የሆነ ልዩ ማንነት ገንብቶ ማደጉን ለታዳሚዎች አብራርተዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ «አፍተር ዘ ሰንሴት» እና «አንደር ዘ ኦፕን ስካይ» የተሰኙ ሁለት የጃፓን ፊልሞች ለዕይታ ቀርበዋል። ቀድሞ ስለታየው «አፍተር ዘ ሰንሴት» የተሰኘ ፊልም ማብራሪያ የሰጡት ምክትል አምባሳደሩ፣ ፊልሙ ከቶኪዮ ግርግር ርቃ በምትገኝ አነስተኛ ደሴት ላይ የምትኖር ቤተሰብን የወላጅና የልጅ ግንኙነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አጋራ

YouTube

አማEN