ወላይታ ድቻ ለሁለተኛ ጊዜ ቅጣት ተጣለበት
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የውድድር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ በሊጉ የስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በታዩ የዲሲፕሊን ጉድለቶች ዙሪያ የቅጣት ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ

ወላይታ ድቻ በአዲስ አበባ ስታዲየም በኢትዮጵያ ቡና 2 ለ 1 በተሸነፈበት መርሃግብር ከዕረፍት መልስ ከ66ኛው ደቂቃ በኋላ የቡድኑ ደጋፊዎች የውሀ ፕላስቲኮችን ወደ ሜዳ በመወርወራቸው እና አንድ ወንበር እንዲሰበር በማድረጋቸው የ75 ሺህ ብር እና የተሰበረውን ወንበር እንዲያሰራ የሚል ቅጣት ሲጣልበት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ደግሞ ሁለት ወንበር በመስበራቸው እንዲያሰሩ አልያም ተሰልቶ በሚወጣው ዋጋ መሠረት እንዲከፍሉ ተወስኗል።
በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ነገሌ አርሲ ጋሞ ጨንቻን በረታበት ጨዋታ ጨዋታው አራት ደቂቃዎች ዘግይቶ እንዲጀመር ነገሌዎች ምክንያት በመሆናቸው የ15 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት በክለቡ ላይ ሲጣል በጨዋታ ሳምንቱም ላይ የወልዋሎ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የቡድናቸው አምስት ተጫዋቾች ቢጫ በማየታቸው የአምስት ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎላቸዋል።
