በ7 ጨዋታዎች 95 ደቂቃ ብቻ የተጫወተው ጋርናቾ መጨረሻው ምን ይሆን?
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አስቶን ቪላ በጋላታሳራይ 1 ለ 0 ሲሸነፍ የ22 ዓመቱ አርጀንቲናዊ የመስመርተጫዋች አሌሃንድሮ ጋርናቾ ከስብስብ ውጪ መደረጉን ተከትሎ፤ የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ እና የቼልሲ ኮከብ በቪላ ያለው ቆይታ አጠያያቂ ሆኗል።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 3
ከሶስት ዓመት በፊት በኢስታንቡል በተደረገ የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ለማንቸስተር ዩናይትድ የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሮ እና በኋላም የኤፍ.ኤ ካፕ ዋንጫ በማንሳት ድንቅ ብቃት አሳይቶ የነበረው አሌሃንድሮ ጋርናቾ፤ በዘንድሮው የውድድር ዘመን አስቶን ቪላ ቢቀላቀልም በመጀመሪያ አሰላለፍ አንድም ጨዋታ አልጀመረም።
በሁሉም ውድድሮች በሰባት ጨዋታዎች 95 ደቂቃዎችን ብቻ የተጫወተው እና በጋላታሳራይ ጨዋታ 12 ተቀያሪዎች ማስመዝገብ ሲቻል ኤምሪ 11 ብቻ መርጠው ጋርናቾን ሳያካትቱ ቀርተዋል፡፡
ባለፈው የውድድር ዘመን ሃርቪ ኤሊዮት በውሰት መጥቶ በተመሳሳይ ሁኔታ ከተገለለ በኋላ፣ አሁን ደግሞ በ43 ሚሊዮን ፓውንድ የግዴታ የዝውውር ግዢ አማራጭ የተገኘው ጋርናቾ ከስብስብ ሲወጣ፤ ጋርናቾም በኢንስታግራም ገጹ የአስቶን ቪላን መረጃዎች ሙሉ በሙሉ ማጥፋቱ ግንኙነቱ እየሻከረ መምጣቱን ያሳያል።
አስቶን ቪላ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች በአራቱ ግብ ማስቆጠር ተስኖት በማጥቃት ክፍል ቢቸገርም፣ ኤምሪ እንደ ኢሚሊያኖ ቡዌንዲያ፣ ጆን ማክጊን እና ወጣቶቹ አሊሰን እና ኢብራሂም ንባዬ ያሉ ተጫዋቾችን በማስቀደም ጋርናቾን ከእቅዳቸው ውጪ አድርገውታል። ይህም የክለቡን የውሰት ዝውውር ስትራቴጂ እና የወደፊት ተጫዋቾችን የመሳብ አቅም ጥያቄ ምልክት ውስጥ ከቷል።
