የአብያታ-ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ የጎብኚዎች ቁጥር መሻሻሉ ተገለጸ
በተፈጥሯዊ ውበቱና ባለው ብዝኃ-ሕይወት ሰፊ የቱሪዝም መዳረሻ የመሆን እምቅ አቅም እንዳለው የሚታመነው የአብያታ-ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ በዓመት ወደ 8 ሺህ የሚጠጉ ጎብኚዎችን እንደሚያስተናግድና በጎብኚዎች ቁጥር ረገድ መሻሻል እንዳሳዬ የፓርኩ ምክትል ኃላፊ ሜኤሶ ሀምዲኖ ከሀገሬ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገለጹ።
ዜና ክፍል · · 2 ደቂቃ ንባብ

ምንም እንኳን ካለፉት ጊዜያት አንፃር የቱሪስቶች ቁጥር መሻሻል ያሳየ ቢሆንም እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ የአብያታ-ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ ካለው ከፍተኛ የተፈጥሮና የቱሪዝም ሀብት አንፃር ከፓርኩ አቅም ጋር የሚመጣጠን ገቢ እያገኘ አይደለም።
ከአውሮፓ፣ ከእስያና ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ወደ ፓርኩ የሚመጡ ቱሪስቶች በዋናነት ለአዕዋፍ ምልከታ የሚመጡ ሲሆኑ ከአዕዋፍ ባሻገር የተፈጥሮ ፍል ውኃ እንፋሎትና ሙቀት እንዲሁም በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የዱር እንስሳት ቱሪስቶችን የሚስቡ ሀብቶች ናቸው።
አቶ ሜኤሶ ሀምዲኖ እንደጠቆሙት በዓመት ከፓርኩ ከ300,000 እስከ 400,000 ብር የሚጠጋ ገቢ ብቻ የሚገኝ ሲሆን የመግቢያ ክፍያው ዝቅተኛ መሆኑ ለፓርኩ አነስተኛ ገቢ አንዱ ምክንያት ነው።
የአገር ውስጥ ጎብኚም ሆነ የውጭ አገር ቱሪስት ከአንድ ዶላር በታች አነስተኛ ክፍያ እንደሚከፍልም ተገልጿል። አቶ ሜኤሶ አክለውም በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣው የቱሪዝም ክፍያ ማሻሻያ ሕግና ደንብ በተግባር በሚፈለገው ደረጃ ባለመተግበሩ ፓርኩ ያለውን ሀብት በአግባቡ ለማስተዳደርና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ውስንነት እንደፈጠረ አመልክተዋል።
አብያታ-ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ በኦሮሚያ ክልል ነጌሌ አርሲ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን በ1963 ዓ.ም የተመሠረተ ከፊል በረሃማ ጥብቅ ስፍራ ነው። ፓርኩ ሦስት ኪሎ ሜትር በሚረዝም ኮረብታ የተለያዩትን የአብያታና የሻላ ሐይቆች እንዲሁም የጭቱን ሐይቅ ያጠቃልላል።
በግዙፍ የእሳተ ገሞራ የተፈጠረው የሻላ ሐይቅ 260 ሜትር በሚጠጋ ጥልቀቱ በኢትዮጵያ ጥልቁ ሀይቅ ሲሆን ሰማያዊ-ጥቁር መልክ ባለው ውሀና በሰባት ደሴቶቹ ለውኃ ላይ አዕዋፍ እንደ ማደሪያና መራቢያ ስፍራ ሆኖ ያገለግላል።
በሌላ በኩል በጥልቀቱ አነስተኛና ከፍተኛ የጨዋማነት ይዘት ያለው የአብያታ ሐይቅ የጨው ክምችቱ ከፍተኛ በመሆኑ የዓሣ ሀብት ባይኖረውም ከጭቱ ሐይቅ ጋር ለአዕዋፍ እንደ ዋነኛ መመገቢያ ስፍራ ያገለግላል።
በሻላ ሐይቅ አካባቢ የሚገኘው ትልቁ ፍል ውኃ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስና የሙቀት መጠኑ 67 ዲግሪ ሴልሺየስ የሚደርስ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎችም በተለይ ከነሐሴ እስከ ጥቅምት ባሉት ወራት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ስፍራው በመምጣት ውኃውን ለባህላዊ ሕክምናና ለጤና እንክብካቤ ይጠቀሙበታል።
ከኢትዮጵያ የአዕዋፍ ሀብት 63 በመቶ ያህሉን የሚይዘው ፓርኩ 463 የሚደርሱ የአዕዋፍ ዝርያዎችን ያስጠለለ ሲሆን በየዓመቱ ከ140 በላይ ስደተኛ የአዕዋፍ ዝርያዎች ከአውሮፓ፣ ከእስያና ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ይመጣሉ። ፍላሚንጎዎች፣ ግሬት ዋይት ፔሊካኖችና በልዩ ሁኔታ ተከልሎ ጥበቃ የሚደረግለት የሰጎን ማርቢያ ዋነኞቹ የፓርኩ መገለጫዎች ናቸው።
