ወደ ዋናው ይዘት ዝለል

የአዲስ አበባ ከተማ አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫል ተጀመረ

"የባህል ስፖርቶቻችን በብዝኃነት ለደመቀች፤ በምክክር ለጸናች ኢትዮጵያ!" በሚል መሪ ቃል 17ኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማ አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫል በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።

ዜና ክፍል · · 2 ደቂቃ ንባብ · 1

በሲኞሬ ሜዳ በተካሄደው መክፈቻ የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ ሶፍያ አለሙ፤ በቅርቡ የሚከበርው 21ኛው የሕዝቦች የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መንፈስ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ተሳታፊዎቹ በባህል ስፖርቶቹ አማካኝነት የብሔረሰቦችን ማኅበራዊ እሴቶች፣ መከባበር እና አብሮነት በተግባር እያንጸባረቁ በመሆኑ ለባህል ስፖርቶች እድገት በቀጣይ ከፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ በመተባበር እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

የአፍሪካ ባህል ስፖርቶችና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ህይወት መሀመድ ከተማ አስተዳደሩ ለባህል ስፖርቶች እድገት ልዩ ትኩረት በመስጠት ከታዳጊዎች ፕሮጀክት፣ ከውድድር እንዲሁም ከስልጠና አኳያ በሁሉም ክፍለ ከተሞች በርካታ ውጤታማ ስራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

አዲስ አበባ ለተለያዩ አህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ መድረኮች ምቹ በመሆኗ ኢትዮጵያ በባህል ስፖርት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄዱትን ሁለት ታላላቅ አህጉር አቀፍ መድረኮች ማለትም የፊታችን ታህሳስ 1 እና 2/2019 ዓ.ም የአፍሪካ ባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ሲምፖዚየም እንዲሁም የፊታችን ሚያዚያ የመጀመሪያው የአፍሪካ ባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች መልቲ ኤቨንት ፌስቲቫል በታላቅ ድምቀት የምታስተናግድ መሆኗን ተናግረዋል።

ፕሬዝደንቷ ለባህል ስፖርቶች ሁለንተናዊ እድገት እንዲሁም ምቹ መሠረት ልማቶችን በማሟላት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ለሚገኙት የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፤ ለአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እና ለከተማ አስተዳደሩ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እንዲሁም ለከተማዋ ነዋሪዎች በሙሉ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ ስፖርቱን ለማህበራዊ ትስስር፣ ለቱሪዝምና ለስፖርት ዲፕሎማሲ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ከኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጋር በቀጣይ ስራዎችን ለመስራት መታቀዱን ተናግረዋል

ውድድርና ፌስቲቫሉ በሐዋሳ ከተማ ለሚካሄደው ለ24ኛው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውድድር እና 20ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል የቅድመ ዝግጅት አካል ሆኖ የሚካሄድ ይሆናል።

አጋራ

YouTube

አማEN