ዴክላን ራይስ ከአርሰናል ጋር የአምስት ዓመት አዲስ ኮንትራት ለመፈራረም በመርህ ደረጃ ተስማማ !
እንግሊዛዊው የአርሰናል አማካይ ዲክላን ራይስ እስከ 2031 ድረስ በክለቡ እንዲቆይ የሚያደርገውን የአምስት ዓመት አዲስ ኮንትራት በመርህ ደረጃ መስማማቱ ታውቋል።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ

በዚህ አዲስ ስምምነት መሰረት ራይስ በክለቡም ሆነ በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ያለውን ከፍተኛ ደረጃ የሚመጥን የደመወዝ ጭማሪ ያገኛል ተብሏል።
ራይስ በ2023 ከምሥራቅ ለንደኑ ክለብ ዌስትሃም በ105 ሚሊዮን ፓውንድ ነበር ወደ አርሰናል የተዘዋወረው።
የአሁኑ ኮንትራቱ በቀጣዩ የውድድር ዘመን መጨረሻ የሚጠናቀቅ ቢሆንም፣ አርሰናል ኮንትራቱን በአንድ ዓመት የማራዘም አማራጭ ነበረው።
ሆኖም ራይስ እና ክለቡ ከዚያ በፊት በአዲስ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይፋ ሆኗል።
ራይስ እንደሚለው “ሁልጊዜ ለራሴ ኢላማ የማስቀምጥ እና ለበለጠ ነገር የምጥር ተጫዋች ነኝ። በተጫወትኩባቸው ክለቦች ሁሉ የተረጋጋሁ ነበርኩ። አዲስ ኮንትራት በቅርቡ እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል ።
ዴክላን ራይስ አክሎም “አሰልጣኙ ከፍተኛ እምነት በሚጥልብኝ እና ብዙ የቡድን አጋሮቼ ከፍተኛ ጉልበት እና ጥረት በሚያደርጉልኝ እንደ አርሰናል ባለ ክለብ ውስጥ በመገኘቴ እጅግ እድለኛ ነኝ።ይህም እግር ኳስ መጫወትን በጣም ቀላል ያደርገዋል” ሲል ገልጿል።
