በ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዛሬ ዘጠኝ ሀገራት ቀድመው ለማለፍ ወሳኝ ጨዋታዎችን ዛሬ ያደርጋሉ
ኬንያ፣ ታንዛንያ እና ዩጋንዳ በጋራ ለሚያስተናግዱት የ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረገው የማጣሪያ ውድድር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ዛሬ ማክሰኞ በሚደረጉ የምድብ የ4ኛ ጨዋታዎች፣ ዘጠኝ የአፍሪካ ሀገራት ቀድመው ወደ ፍጻሜው ውድድር የማለፍ እድል አላቸው።
ዜና ክፍል · · 2 ደቂቃ ንባብ · 17

እስካሁን ባደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ሙሉ 9 ነጥብ በመሰብሰብ 100 በመቶ የማሸነፍ ዉጤት ያላቸው ሞሮኮ፣ ኮትዲቯዋር፣ ማሊ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዚህ 4ኛ ዙር ጨዋታ ድል የሚቀናቸው ከሆነ የመጀመሪያዎቹ አላፊ ሀገራት ይሆናሉ፦
👉ሞሮኮ (ምድብ 1): ኒጀርን 5 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት የረታችው ሞሮኮ፣ ዛሬ በድጋሚ ከኒጀር ጋር ስትጫወት ካሸነፈች ማለፏን ታረጋግጣለች።
👉ኮትዲቩዋር (ምድብ 3): በሜዳወኡ ጋምቢያን 2 ለ 1 ያሸነፈዉ የሄርቬ ሬናርድ ቡድን፣ ወደ ጋምቢያ ተጉዞ የሚያሸንፍ ከሆነ ትኬቱን ይቆርጣል።
👉 ማሊ (ምድብ 11): ሩዋንዳን 3 ለ 2 በሆነ ድራማዊ ውጤት ያሸነፈችው ማሊ፣ ዛሬ በኪጋሊ ሩዋንዳን በድጋሚ ከረታች ቀድማ ታልፋለች።
👉ዲ.ሪ. ኮንጎ (ምድብ 5): ሴራሊዮንን በመልሱ ጨዋታ የምታሸንፍ ከሆነ የሴባስቲያን ዴሳብሬ ቡድን ማለፉን ያረጋግጣል።
👉7 ነጥብ በማያዝ በሌሎች ውጤቶች ታግዘው ሊያልፉ የሚችሉ ሀገራት
በ7 ነጥብ ምድባቸውን እየመሩ የሚገኙት ግብፅ፣ አንጎላ፣ ቤኒን፣ ቡርኪናፋሶ እና ካሜሩን በራሳቸው ድል እና በተጋጣሚዎቻቸው ውጤት መሰረት ቀድመው የማለፍ እድል አላቸው፦
👉ግብፅ እና አንጎላ (ምድብ 2): ማላዊን 5 ለ 0 ያሸነፈችው ግብፅ ወደ ማላዊ ተጉዛ ስትጫወት፣ አንጎላ ደቡብ ሱዳንን ዛሬ ትገጥማለች። ሁለቱም ሀገራት ካሸነፉ ሁለት ጨዋታ እየቀራቸው በጋራ ያልፋሉ።
👉ቤኒን እና ቡርኪናፋሶ (ምድብ 6): ቤኒን ትናንት ሰኞ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክን ገጥማ ስላሸነፈች፣ ቡርኪናፋሶ ዛሬ ማክሰኞ ከሞሪታንያ ላይ 3 ነጥብ ከወሰደች ሁለቱም ተያየእዘዉ እንዲያልፉ ያስችላቸዋል።
👉ሌሎች ተጠባቂ ጨዋታዎች
አልጄሪያ ወደ ቶጎ ተጉዛ የምትጫወት ሲሆን፣ ናይጄሪያ ደግሞ በታንዛንያ ሜዳ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ለማሳካት ትፋለማለች። ከሰኔ 12 እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2019 ዓ.ም የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ ሁለት የማጣሪያ ዙሮች በመጋቢት 2019 ዓ.ም የሚደረጉ ይሆናል።
