“ በአርሰናል የዝውውር ፍላጎት ጫና ተሰምቶኝ ነበር” ቪኒሲየስ ጁኒየር
ብራዚላዊው ኮከብ ቪኒሲየስ ጁኒየር በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ያሳየው ደካማ አቋም በከፊል በክረምቱ ከሪያል ማድሪድ ሊለቅ ይችላል በሚል በተነሱ ወሬዎች ከፍተኛ ጫና ስለተሰማው መሆኑን አምኗል።
ዜና ክፍል · · 2 ደቂቃ ንባብ · 2

የ26 ዓመቱ የፊት መስመር ተጫዋች የኮንትራቱ የመጨረሻ 12 ወራት ሲቃረብ የአርሰናል የዝውውር ኢላማ የነበረ ቢሆንም፣ በነሐሴ ወር እስከ 2032 ድረስ በሳንቲያጎ በርናባው የሚያቆየውን አዲስ የረጅም ጊዜ ኮንትራት ለመፈረም መምረጡ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ብራዚል ከዓለም ዋንጫ በጥሎ ማለፉ 16 ውስጥ መሰናበቷ እና የዝውውር ጭምጭምታዎቹ ተዳምረው፣ በዚህ የውድድር ዘመን ለሪያል ማድሪድ ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ እንዲያስቆጥር ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ተሰምቶታል።
ቪኒ እንደሚለው “የዓለም ዋንጫው ለሁሉም ብራዚላውያን ያለው ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ፣ ከውድድሩ በኋላ የምችለውን ያህል በደንብ የተዘጋጀሁ አይመስለኝም” ሲል ተናግሯል።
“ይህን ያህል ቀድመን ከውድድሩ መውጣታችን ያልጠበቅነው ነገር ነበር። ስለዚህ እረፍቴን ለመዝናናት፣ ለማረፍ እና ከቤተሰቦቼ ጋር ተጨማሪ ጊዜ ለማሳለፍ ተጠቀምኩበት። ከቀደሙት ዓመታት ያነሰ ልምምድ ነው የሰራሁት፤ ያ ደግሞ የውድድር ዘመኑን አጀማመሬን ጎድቶት ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ፣ ከኮንትራት እድሳቴ ጋር በተያያዘ ባለፈው ክረምት በርካታ ክለቦች ፍላጎት በማሳየታቸው እና በሪያል ማድሪድ በነበረው ሁኔታ እውነት ለመናገር በጣም ተጨንቄ ነበር። ነገር ግን የውድድር ዘመኑ ገና በጣም ረጅም ነው” ብሏል።
ቪኒሲየስ ባለፈው ወር ከቪያሪያል ጋር በተደረገ ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ የአራት ጨዋታ ቅጣት የተጣለበት ሲሆን በእርሱ አለመኖር ያን ዲዮማንዴ በብራዚላዊው ተመራጭ የግራ መስመር ቦታ ላይ ለሪያል ማድሪድ ደምቆ መታየት ችሏል።
እንደ ቪኒ ገለፃ “ይህን ያህል ከፍተኛ ደረጃን ለረጅም ጊዜ ማስቀጠል ሁልጊዜም በጣም ከባድ ነው፣ይህንን ለብዙ ዓመታት ማድረግ እና ተመሳሳይ ቁጥሮች ላይ መድረስ የቻሉት ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ሊዮኔል ሜሲ ብቻ ይመስሉኛል። እኔ ሰው ነኝ፣ ብዙ ጊዜ ስህተቶችን እሰራለሁ፣ ነገር ግን ሁልጊዜ ለመሻሻል እጥራለሁ።” ብሏል።
