ወደ ዋናው ይዘት ዝለል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ የ3 ወራት ሪፖርት ካርድ እና 8 ቡድኖች- 25 ጨዋታዎች

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለፉት ሦስት ወራት ተመሳሳይ ወረቀት ይዞ መጥቷል። ስምንት ቡድኖች፣ 25 ጨዋታዎች፤ ከሴቶች ኦሊምፒክ ቡድን በስተቀር እስካሁን ግባቸውን ያሳኩ የሉም። ከታች ያለው ካርድ ከነሐሴ አጋማሽ እስከ ትላንቱ የባሕር ዳሩ ጨዋታ የተመዘገበውን ውጤት ቡድን በቡድን ያሳያል፤ ያሸነፍነውን፣ አቻ የወጣነውን፣ የተሸነፍነውን፣ ያገባነውንና የገባብንን መዝግቦ ያሳያል።

በሳሙኤል ስለሺ · · 5 ደቂቃ ንባብ · 1

ቁጥሮችን በሰንጠረዥ ማንበብ ይደክማል፤ አንድ ወረቀት ግን ሁላችንም በደንብ እናውቀዋለን። ከትምህርት ቤት ወደ ቤት የሚመጣው የውጤት ካርድ። ተማሪ ሲሰጠው ልቡ የሚመታበት፣ ልጁ አንገቱን ደፍቶ የወላጁን መልስ የሚጠብቅበት ወረቀት።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለፉት ሦስት ወራት ተመሳሳይ ወረቀት ይዞ መጥቷል። ስምንት ቡድኖች፣ 25 ጨዋታዎች፤ ከሴቶች ኦሊምፒክ ቡድን በስተቀር እስካሁን ግባቸውን ያሳኩ የሉም። ከታች ያለው ካርድ ከነሐሴ አጋማሽ እስከ ትላንቱ የባሕር ዳሩ ጨዋታ የተመዘገበውን ውጤት ቡድን በቡድን ያሳያል፤ ያሸነፍነውን፣ አቻ የወጣነውን፣ የተሸነፍነውን፣ ያገባነውንና የገባብንን መዝግቦ ያሳያል።

በካርዱ ጥግ ላይ አንድ የቀይ ማኅተም አለ። «ከፍተኛ ክትትል ያስፈልገዋል» ይላል። ካርዱን እንደ ወላጅ ያንብቡት፤ ምክንያቱም ተጠያቂነቱ ሜዳ ላይ ባሉት ልጆች ላይ ብቻ መውደቅ የለበትም።

👉የውጤት ካርዱ

ከነሐሴ አጋማሽ እስከ ትናንትናው የባሕር ዳር ጨዋታ ድረስ ኢትዮጵያን ወክለው ወደ አህጉራዊ መድረክ የወጡት ዋናው ብሔራዊ ቡድን፣ ከ23፣ ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች ቡድኖች፣ የሴቶች ኦሊምፒክ ቡድን፣ ሁለት የወንዶች ክለቦችና አንድ የሴቶች ክለብ ናቸው። ሁሉም አንድ ህልም ይዘው ወጡ፤ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መድረስ፣ ወደ ኦሊምፒክ ማለፍ፣ ወደ ካፍ የክለቦች ውድድር ምድብ ድልድል ውስጥ መግባት። ዛሬ ያ ህልም በእጁ ያለው በአንድ ቡድን ብቻ ነው፤ በሴቶች ኦሊምፒክ ቡድን።

ዋናው ቡድን እጣ ፈንታውን በሌሎች ሜዳዎች ውጤት ላይ አድርጓል፤ አሁን የሚጠብቀው ሞዛምቢክ ደጋግማ እንድትሸነፍ እና የእሱን ደጋግሞ ማሸነፍ ነው። ከ23 ዓመት በታች ቡድን የመጀመሪያውን ዙር ያለፈው ሜዳ ላይ ሳይሆን በፎርፌ ነበር፤ ሞሮኮ ፊት ግን በደርሶ መልስ ወደቀ። ከ20 ዓመት በታች ቡድን ምድቡን በመጨረሻ ደረጃ አጠናቆ ሳይሳካለት ቀረ። ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ ከሦስት ጨዋታ ሁለቱን ተሸንፎ ወጣ።

ሲዳማ ቡናና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያውን ዙር የካፍ ክለቦች ውድድር ተሻግረው ሁለተኛው ላይ ሲደርሱ በድምሩ አንድ ጎል አስቆጥረው አሥራ ሁለት ተቆጥሮባቸው ከውድድሩ ተባረሩ። ንግድ ባንክ ሴቶች ሁለት ጨዋታዎችን በትልቅ ልዩነት አሸንፈው ጭብጨባ ቢያገኙም፣ ዋጋ በነበራቸው ሁለት ጨዋታዎች ወድቀው በሴካፋ ሦስተኛ ወጡ፤ የቻምፒየንስ ሊጉ በር ፊት ቆመው ቀሩ።

ይህ ሁሉ እንግዲህ በፊፋ ከ15 አመት በታች የአለም ዋንጫ እና ፌስቲቫል ውድድር ላይ የደረሰብንን ተደጋጋሚ ሽንፈት ሳንቆጥር ነው።

የነገሩን ውስብስብነት አጉልቶ የሚያሳየው ደግሞ የገጠምናቸውን ቡድኖች ስንመለከት ነው። ዋናው ብሄራዊ ቡድኑ ከገጠመው ሴኔጋል እና የ23 አመት በታች ቡድኑ ከገጠመው የሞሮኮ ቡድን ውጭ ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ ደካማ እግር ኳስ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ናቸው። ጂቡቲ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቻድ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ሊቢያ፣ ታንዛኒያ። በዚህ ደረጃ ተወዳድረን ነው እንደዚህ አይነት ውጤት ያስመዘገብነው።

የወንዶቹን ብቻ ከወሰድን ካደረጓቸው 19 ጨዋታዎች 4 አሸንፈን 13 ተሸንፈናል። በ19 ጨዋታ 15 ጎሎችን ብቻ አስቆጥረን 34 ተቆጥሮብናል፤ በ19 ጨዋታዎች ለትውልድ የተላለፈ 19 የግብ እዳ አለብን። ይህ ማለት 2.27ጎሎች ከተቆጠሩብን በኋላ ነው አንድ ጎል የምናስቆጥረው። ብሄራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች 1 ግብ ብቻ አስቆጥሯል፤ በሜዳው የባህርዳር ስቴዲየም በ180ደቂቃ ምንም ግብ አላስቆጠረም።

ይህ በውጤት ሰሌዳ ላይ ተጽፎ የሚቀር ሽንፈት ብቻ አይደለም። ለዓመታት ሜዳ ዳር ቆሞ የጠበቀውን ደጋፊ ያሳዝናል። ልጁን እጅ ይዞ ወደ ስታዲየም የወሰደ አባት ከሜዳ ሲመለስ ምን እንደሚለው ያጣል። ቀና ብሎ መሄድ የሚፈልግ ትውልድን አንገት ይሰብራል። ደግሞ ከሽንፈት በላይ የሚያመው ደካማ ተብሎ መታየት ነው፤ ሽንፈት ይረሳል፣ ስም ግን ይቀራል።

ቁጥሮቹን በተፈለገው የሂሳብ ስሌት ብናሰላቸው ውጤቱ ድክመታችንን ብቻ የሚናገር ነው። የገጠምናቸው ቡድኖች፣ ቦታዎች፣ ዳኞች፣ የአየር ሁኔታዎች ሁሉ የተለያዩ ናቸው። የተገኘው ውጤት ግን አንድ እና አንድ ነው፤ ሽንፈት፣ ደካማ ሆኖ መታየት፣ የማንችል ሆኖ መገኘት። ህዝብን ማሳዘን፣ የትውልድን አንገት መስበር፣ ቀና እንዳንል ማድረግ።

ሦስት ወር ሙሉ ባንዲራችንን ተሸክመው የሄዱ ልጆች ባዶ እጃቸውን ሲመለሱ ማየት ያመናል። የሚያስቆጨው ግን ሽንፈቱ ብቻ አይደለም፤ ሽንፈቱ እንደ ዜና መሆኑ ቀርቶ እንደ ልማድ መታየት መጀመሩ ነው።

ተጫዋቾቹ የተለያዩ ናቸው፤ አሰልጣኞቹም፣ ክለቦቹም፣ የዕድሜ ደረጃዎቹም የተለያዩ ናቸው። የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ግን አለ፤ ሁሉም የወጡት ከአንድ የእግር ኳስ ሥርዓት ነው። ይህ ሁሉ የሆነው በአሰላለፍ ስህተት ነው ብለን አናምንም፣ በተጨዋች ቅያሪ ድክመት የመጣም አይደለም፤ አሰልጣኙ ቁጭ ብለው ስለመሩ ወይም ቆመው ስላላበረታቱም አይደለም፤ ኢንፋንቲኖ ለፕሬዚደንቱ ስልክ ስላልደወሉ- ደብዳቤም ስላልፃፉ አይደለም፤ ይህ ሁሉ ሽንፈት የስርዓት ውጤት ነው።

👉ዘሩን የዘራው ማን ነው?

ጥያቄው ከእንግዲህ «ለምን ተሸነፉ?» አይደለም፤ «ይህን የሽንፈት ሥርዓት ማን ፈጠረው?» የሚል ነው፤ ከእሱም ቀጥሎ «ይህን ሥርዓት ማን ይጠይቀው?» የሚለው ይመጣል። ችግኙን የተከሉት፣ ተክለው ካበቁ በኋላም እየተንከባከቡ ያሳደጉት ሰዎች ዛሬም የእግር ኳሱ መሪ ተዋናዮች ሆነው መቀጠላቸው ደግሞ ለሌላ የ25 ጨዋታዎች ውርደት እያዘጋጀን መሆኑን ያሳያል።

ከዚህ ሁሉ ሽንፈት በስተጀርባ ያልተሰሩ የቤት ሥራዎች ተቆልለው ይገኛሉ፤ እነሱም በክልል፣ በከተማና በብሔራዊ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ አዳራሾች ውስጥ ናቸው። እግር ኳስ ማንም መጥቶ እንዲታበይበት መንገድ የከፈቱ፣ በጉባኤው ድምጽ ሲቆጠር ከፍ ብለው የተዘረጉ ክንዶች፣ እጅ መንሻ ተቀብለዋል ተብለው የሚታሙ እጆች፣ ብር የቆጠሩ ጣቶች የዚህ ሥርዓት ባለቤቶች ናቸው።

ሌላው የቤት ሥራ ደግሞ በክለቦች ቢሮዎች ውስጥ ይገኛል፤ በብሔርና በአካባቢ ተቧድነው ከረዥም ጊዜ የእግር ኳስ ልማት ይልቅ ለጊዜያዊ ስሜት የተንበረከኩ፣ በተጨዋች ዝውውርና በአሰልጣኝ ቅጥር የሚታሙ የክለብ አመራሮች ይህን ሥርዓት ከፈጠሩት መካከል ናቸው።

በክለቦቹ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች፣ አሰልጣኞችና ተጨዋቾችም ቢሆኑ ከተጠያቂነት ነጻ አይደሉም፤ «እንጀራ ነው» በሚል ምክንያት ዝም ብለው ይህ መጥፎ ሥርዓት እንዲጠናከር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ስለዚህ ይህ የ25 ጨዋታዎች፣ የሦስት ወራት ውጤት በአጋጣሚ የመጣ አይደለም፤ የዛሬ አሥር እና አስራ አምስት ዓመት የዘራነው ዘር የደረሰ ፍሬ፣ በዚያን ጊዜ ያልሠራነው ሥራ የተከማቸ ዕዳ ነው። ዛሬም ዘር ካልዘራን ከአሥር ዓመት በኋላ የሚጽፈው ሰው ተመሳሳይ ሰንጠረዥ ይዞ ይመጣል።

👉መደምደሚያ

በየትኛውም ትምህርት ቤት ውስጥ የውጤት ካርድ በዚህ አያበቃም። ወላጅ ይፈርምበታል፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ካርድ ግን እስካሁን የፈረመበት የለም። ማንም «ይህ የእኔ ኃላፊነት ነበር» ያለ አልሰማንም። በካርዱ ጥግ ላይ ያለው የቀይ ማኅተም ከሜዳ ላይ ልጆች ይልቅ ሥርዓቱን ይጠቁማል፤ ምክንያቱም ጎል ያላስቆጠሩት ተጫዋቾች ሳይሆኑ ተጫዋቹን ያፈራው ሥርዓት ነው «ከፍተኛ ክትትል» የሚያስፈልገው።

ክትትሉ ደግሞ ከእኛ፣ ከደጋፊዎች፣ ከጋዜጠኞችና ከባለሙያዎች መጀመር አለበት። ፌዴሬሽኑ የውጤት ግምገማ ሪፖርቱን ለህዝብ ያቅርብ። የልማት በጀቱ ምን ላይ እንደዋለ ይታይ። የአሰልጣኞችና የአመራሮች ሹመት መስፈርት ይፋ ይሁን። እነዚህን ጥያቄዎች ዛሬ ካልጠየቅን፣ ሦስት ወር ቆይቶ በሚመጣው ቀጣይ ካርድ ላይ ተመሳሳይ ቁጥሮችን፣ ምናልባትም የባሰ ውጤት እናነባለን።

እናንተ ፍረዱ።

አጋራ

YouTube

አማEN