“የ2019 በጀት ዓመት እቅድ በፍትህና በተቋማት ቁጥጥር ላይ ያተኩራል”
በ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል ተቋማትን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ፣ የፓርላማ ዲፕሎማሲን፣ የህዝብ ውክልናንና ህገ መንግስታዊና ምክር ቤታዊ ማእቀፎችን ማጠናከር በእቅድ መያዙ ተገለጸ።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 2

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታርጃት ደበል እቅዱ የምክር ቤቱን አራት ተልዕኮዎች፣ ተጠሪ ተቋማትንና የመደመር መንግስት ስትራቴጂ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል። አክለውም ለሕግ ማውጣት ቅድሚያ በመስጠት የፍትህ ስርዓቱን ለማሳለጥና ሀገራዊ አንድነትንና ህብረ ብሔራዊነትን ለማጠናከር እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ በሚካሄዱ የመስክ ምልከታዎች የተቋማት አፈፃፀም፣ የሰብዐዊ መብቶች አያያዝና የበጀት አጠቃቀም እንደሚረጋገጥ ተጠቁሟል። እንዲሁም የ3 ዓመቱ የፍትህ ትራንስፎርሜሽንና የፍርድ ቤቶች የለውጥ ፍኖተ ካርታ አተገባበር ክትትል ይደረግባቸዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላትም እቅዱን ውጤታማ ለማድረግ ከምንከታተላቸው ተቋማት ጋር መነጋገር ለተግባራዊነቱ ያግዛል ሲሉ ገልጸዋል። በተጨማሪም አባላቱ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ መሰረታዊ የህግ ስልጠና እንዲያገኙ ማመቻቸት እንደሚገባ ተመላክቷል።
