የኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት አባልነት የአቪዬሽን ደኅንነትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተገለጸ
ኢትዮጵያ በሞንትሪያል ካናዳ በተካሄደው የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) 43ኛ ልዩ ጉባኤ የድርጅቱ ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ተልዕኮን ለማሳካት እገዛ እንደሚያደርግ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 1

አገልግሎቱ ባስተላለፈው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ጉባኤው የምክር ቤት አባላትን ቁጥር ከ36 ወደ 40 ለማሳደግ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት በተካሄደው ምር፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ብቸኛ ዕጩ ሆና በመቅረብና የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን (AFCAC) አባል ሀገራትን ሙሉ ድጋፍ በማግኘት በከፍተኛ ድምፅ መመረጧን ገልጿል።
ለዚህ ስኬት የተደረገው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የሕግ ማዕቀፎችን በማሻሻል የተከናወኑ ሁለንተናዊ ሪፎርሞችና በአቪዬሽን ደኅንነት የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ተመራጭ እንዳደረጓት ተጠቁሟል።
አባልነቱ ኢትዮጵያ በድርጅቱ የውሳኔ ሰጪነት ሚናዋን እንድታሳድግና አገልግሎቱ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1412/18 የተሰጠውን የአቪዬሽን ደኅንነት የመምራት፣ የማስተባበርና የመቆጣጠር ተልዕኮ ለማሳካት እንደሚያግዝ ተመላክቷል።
በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ2024 እና በ2025 ICAO ባካሄዳቸው ጥልቅ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦዲቶች ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የደኅንነት ስጋትና ክፍተት የሌለባት መሆኑ መረጋገጡን አገልግሎቱ አስታውሷል።
መንግሥት ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ የሚያከናውናቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶች ለማሳካትም ተቋማዊ ቁመናውን እየገነባ መሆኑን አረጋግጧል።
