ወደ ዋናው ይዘት ዝለል

በብዝኃ ሕይወት የደመቀው የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ

​የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምስራቅ ዞን የሚገኝ ሰፊና ውብ የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎችን የሚሸፍን ፓርክ ነው። በ2003 ዓ.ም በብሔራዊ ፓርክነት ተከልሎ ስያሜውን ያገኘው ይህ ፓርክ በደቡብ ምስራቅ ከሚገኙት የአርሲ ተራራ ሰንሰለቶች ተነስቶ በሰሜን ምዕራብ እስከ ስምጥ ሸለቆ ገደል ጫፍ ድረስ ይዘረጋል።

ዜና ክፍል · · 2 ደቂቃ ንባብ

ፓርኩ ከ1,000 ኪሎ ሜትር ስኩዌር በላይ ስፋት ያለው ሲሆን በስምጥ ሸለቆ ወለልና በከፍተኛ የአፍሮ-አልፓይን ተራሮች መካከል ወሳኝ የሥነ-ምህዳር መተላለፊያ ኮሪደር በመሆን ያገለግላል።

​የተራራ ሰንሰለቱ 4,036 ሜትር ከፍታ ያለውን የጭላሎ ተራራ ጨምሮ የካካ ተራራ፣ አርባጉጉ፣ አሉቶ፣ ደራ ዲልፋቀር፣ የጋለማ ተራራ እና ሁንኮሎን ያካትታል።

በፓርኩ የመረጃ ሰሌዳ ላይ እንደሚታየው ፓርኩ በአራት ዋና ዋና ብሎኮች ተከፍሎ ይተዳደራል። ከዴራ 80 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኘው ዴራ ዲልፋቀር ብሎክ፣ 60 ኪ.ሜ ርቀት ያለው ጭላሎ ጋለማ ብሎክ፣ 140 ኪ.ሜ ርቀት ያለው ሆንቆሎ ብሎክ እና 129 ኪ.ሜ ርቀት ያለው ካካ ብሎክ የፓርኩ አራቱ ብሎኮች ናቸው።

​በመልክዓምድር እና በከፍታ ልዩነት ላይ በመመሥረት ፓርኩ በሦስት የዕፅዋት ሥነ-ምህዳሮች የተከፈለ ነው። ዝቅተኛውና ከ2,843 እስከ 3,756 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው ክፍል እንደ ጥድ (Juniperus procera) እና ዝግባ (Podocarpus falcatus) ባሉ ሀገር በቀል ዛፎች የተሸፈነ ነው። መካከለኛው ከ3,202 እስከ 3,985 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው ዞን እንደ አስታ (heather) ያሉ ቁጥቋጦዎች የተደባለቁበት ሲሆን፣ ከ3,576 እስከ 4,008 ሜትር ከፍታ ያለው ክፍል ደግሞ በሳር፣ በጅብራ እና በአበቦች የተሞላ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ የአርሲ ተራሮች ሰንሰለት ለአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ የውሃ ማማ በመሆን ያገለግላል። በሰሜናዊ ተዳፋት የሚገኙት ሀይቆችና ወንዞች ወደ አዋሽ ወንዝ ተፋሰስ ሲፈሱ በደቡባዊ ተዳፋት ያሉቱ ደግሞ የዋቢ ሸበሌ ወንዝን ይቀላቀላሉ።

​ይህ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ ለሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ወሳኝ መጠለያ ነው። በፓርኩ ውስጥ በርካታ የተራራ ኒያላዎች እና የምኒልክ ድኩላዎች የሚገኙ ሲሆን በከፍተኛ አምባዎች ላይም ብርቅዬው ቀይ ቀበሮ ይገኛል። ከእነዚህ በተጨማሪ ቀበሮ፣ ጥንቸል፣ የደጋ አይጦች፣ አጋዘን፣ ነብር፣ አነር፣ ጅብ፣ ጉሬዛ እና ሽኮኮ በፓርኩ ክልል ውስጥ ይኖራሉ።

​በፓርኩ የተለያዩ ሥነ-ምህዳሮች ውስጥ ከ100 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን ፓርኩ ባለው አስደናቂ የተፈጥሮ ገጽታና ብዝኃ ሕይወት ምክንያት ለተራራ ጉዞ፣ ለወፍ ምልከታ እና ለተፈጥሮ ፎቶግራፍ ተመራጭ መዳረሻ ነው።

መረጃዎቹን ከፓርኩ ኃላፊዎች፣ ከVisit Oromia እና ከGlobal Alliance of National Parks የተገኙ ናቸው።

አጋራ

YouTube

አማEN