ወደ ዋናው ይዘት ዝለል

በእናት ደብረ ማርቆስ የህፃናት መንደር የተገነባው የህፃናት መኖሪያ ህንፃ ተመረቀ

በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ለሚገኘው «እናት ደብረ ማርቆስ የህፃናት መንደር» የበጎ አድራጎት ድርጅት የተገነባው የህፃናት መኖሪያ ህንፃ ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

ዜና ክፍል · · 2 ደቂቃ ንባብ

የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ በትረማርያም ዘለቀ እንደገለጹት፤ የህንፃውን አጠቃላይ የግንባታ ወጪ 65 በመቶ የሚሆነውን የሸፈኑት የኦስትሪያ ቪየና ነዋሪ የሆኑት ዶክተር ክላውስ ሪሴንበርገር ናቸው።

ዶክተር ክላውስ በደብረ ማርቆስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፅንስና ማህፀን ስፔሻሊስት በሆኑት ዶክተር አብነት ሲሳይ አማካኝነት በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ባለፉት ዓመታት ከ15 ሚሊየን 191 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ህጋዊ ፈቃድ አግኝቶ በተከራየው ቤት ተጥለው በተገኙ 3 ህፃናት ስራውን የጀመረው ድርጅቱ፤ በአሁኑ ወቅት ከተማ አስተዳደሩ በሰጠው 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ 56 ህፃናትን ተንከባክቦ በማሳደግና በማስተማር ላይ ይገኛል።

በተጨማሪም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በችግር ውስጥ ለሚኖሩ 154 ህፃናት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፣ በከፈተው ትምህርት ቤትም የአካባቢውን ህፃናት ተጠቃሚ ማድረጉን ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

ከህንፃው ምረቃ ጎን ለጎን ለግንባታው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱት ዶክተር ክላውስ ሪሴንበርገር ደማቅ አቀባበል፣ የምስጋና እና የእውቅና መርሃ ግብር ተካሂዷል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አበባው ግዛቸው በከተማ አስተዳደሩና በህፃናቱ ስም ለዶክተር ክላውስ ምስጋና አቅርበዋል። ድርጅቱ የከተማው ህዝብ ሀብት መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባው፤ የከተማው አመራርና ማህበረሰቡ በባለቤትነት ስሜት ድርጅቱን በመደገፍ ለህፃናቱ እናትና አባት ሆነው ሊያሳድጓቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዶክተር ክላውስ ሪሴንበርገር ህፃናቱ የተመቸ ህይወት እንዲኖራቸው መደገፍ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

ቅን ልብ ባላቸው ባለሙያዎች የተመሰረተው ይህ ተቋም የማህበረሰቡ ድርጅት በመሆኑ ባለሙያዎቹ ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎን የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ
የደብረ ማርቆስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፅንስና ማህፀን ስፔሻሊስት ዶክተር አብነት ሲሳይ ተናግረዋል።

ዘገባው የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ነው።

አጋራ

YouTube

አማEN