ኮካ ኮላ የ2027 አፍሪካ ዋንጫ ስፖንሰር ሆነ
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እና ኮካ-ኮላ በኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ በጋራ ለሚዘጋጀው የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ እንዲሁም ለ2028ቱ ውድድር የአጋርነት ስምምነታቸውን ተፈራርመዋል።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 2
ቶታል ኢነርጂ በቀጣይ ዓመት የሚካሄደው ውድድር ዋና የስያሜ ስፖንሰር ቢሆንም ኮካ-ኮላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የካፍ ውድድር በአጋርነት ተቀላቅሏል።
የካፍ ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ ከዚህ አጋርነት የሚገኘው ገቢ በአፍሪካ ለትምህርት ቤቶች እግር ኳስ ልማት እንደሚውል ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ካፍን ሲረከቡ ተቋሙ የ100 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ እንደነበረበትና ተጨማሪ የ100 ሚሊዮን ዶላር የክስ ጥያቄ ቀርቦበት እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን በተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ እንደሚገኝ አሳውቀዋል።
ካፍ ከላጋርዴር ስፖርትስ ጋር የ10 ዓመት የ1 ቢሊዮን ዶላር የስፖንሰርሺፕ እና የቴሌቪዥን ስርጭት መብት ስምምነት አድርጎ የነበር ቢሆንም ስምምነቱ መቋረጡን ፕሬዝደንቱ አስታውሰዋል።
እንደ ሞትሴፔ ገለጻ ካፍ በአሁኑ ወቅት በባንክ 130 ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ ገንዘብ ያለው ሲሆን፣ ለአባል ሀገራት ፌዴሬሽኖች የሚከፈለው ገንዘብ በእያንዳንዱ ሀገር ስታዲየሞችን ለመገንባት እንዲውል ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
የሞትሴፔ የስልጣን ዘመን በንግድና ገቢ ማስገኘት ረገድ በሰፊው ስኬታማ ተብሎ ቢታይም፣ የአፍሪካ ዋንጫን በየአራት ዓመቱ ለማካሄድ ተይዞ የነበረውን ውሳኔ ካፍ ወደኋላ መመለስ ግድ ሆኖበታል። ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ ውድድሩን ይተካል ተብሎ ለታሰበው የአፍሪካ ኔሽንስ ሊግ በቂ የገንዘብ አቅም አለመኖሩ ነው ተብሏል።
በዚሁ ምክምያት የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለት ዓመቱ መካሄዱን የሚቀጥል ሲሆን ውድድሮቹ በ2027፣ 2028፣ 2031 እና 2033 የሚደረጉ ይሆናል።
#digitalhagerie #CAFAFCON2027 #cocacola
