የአፍሪካ ህብረት በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቀረበ
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ ዓሊ ዩሱፍ በደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ሽግግርን ለማፋጠንና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል የተቀናጀ ግብረ-ኃይል በይፋ መመስረታቸውን አስታወቁ።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 1

የህብረቱ፣ የኢጋድ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጋራ የሆነው ይህ ግብረ-ኃይል ሀገሪቱ በለውጥ ሂደት ውስጥ እያለች ያጋጠማትን የጊዜ ገደብ መራዘምና እርግጠኛ አለመሆን ለመፍታት ያለመ ነው።
ሊቀመንበሩ በንግግራቸው የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት የሽግግሩ ዋና መመሪያ መሆኑን በማስታወስ የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት በመተማመንና በአካታች ውይይት ለጋራ ብሔራዊ መግባባት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
በተለይም ሴቶች፣ ወጣቶች እና ሲቪል ማህበረሰቡ በፖለቲካዊ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ግብረ-ኃይሉ በሶስት ወራት የሥራ ዕቅዱ ተግዳሮቶችን በመለየት ተግባራዊ መፍትሄዎችን እንደሚያመጣ የተገለጸ ሲሆን ሁሉም ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዲያከብሩና ከማንኛውም ሰላምን የሚያደፈርስ ድርጊት እንዲቆጠቡ ጥሪ ቀርቧል። መንግሥትም ቃል የገባውን የሰላም ስምምነት በመፈጸም ረገድ የገንዘብና የፖለቲካ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
