“የከተማ ልማት ጥራት የሀገር ምርታማነትና የሰው ልጅ ክብር መገለጫ ነው” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአዲስ አበባ 57 ሄክታር የሚሸፍን አዲስ የኮሪደር ልማት በይፋ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 1

ቀደም ሲል በተጀመሩት ሥራዎች ላይ የተመሠረተው ፕሮጀክቱ፣ ከቦሌ መድኃኔዓለም እስከ እንግሊዝ ኤምባሲና ሞኤንኮ፣ ከቦሌ ትምህርት ቤት እስከ አደይ አበባ ሞዴል መንደር፣ ከኢምፔሪያል እስከ ሻላ ፓርክ፣ ከቺቺኒያ እስከ ቦሌ ሩዋንዳ፣ እንዲሁም ከአደይ አበባ ስታዲየም እስከ ቦሌ መንገድና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ያካትታል።
ዘመናዊና አረንጓዴው ልማት መንገዶችን፣ የእግረኛና የብስክሌት መሥመሮችን፣ የመሬት ውስጥ መሠረተ ልማቶችን፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችንና ከ5,000 በላይ የመኪና ማቆሚያዎችን ይዟል። በተጨማሪም የታደሱ ትምህርት ቤቶችን፣ ቤተ መጻሕፍትን፣ የመጫወቻና የስፖርት ሜዳዎችን፣ ካፌዎችንና ፕላዛዎችን አካቷል።
ሰብአዊ ክብርንና የኑሮ ጥራትን ማዕከል ያደረገው ልማት፣ ከተሞችን የሥራ ፈጠራ፣ የንግድ፣ የዕውቀትና የባህል ማዕከላት በማድረግ ለሕዝብ ቁጥር ዕድገትና ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ የሚሰጥ አረንጓዴ፣ አካታችና የማይበገር ልማት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
