መቶ ብራችንን ያደመቀውን ታሪካዊ የሶፍ ዑመር ዋሻን በአይናችን ተመለከትነው
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት እና በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት የሚከበረውን 21ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ምክንያት በማድረግ በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ የሥራ ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው የሚዲያ ቡድን ታሪካዊውን የሶፍ ዑመር ዋሻ ጎብኝቷል።
ዜና ክፍል · · 3 ደቂቃ ንባብ · 2

አጃኢብ ነው!
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት እና በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት የሚከበረውን 21ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ምክንያት በማድረግ በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ የሥራ ጉብኝት እያደረገ የሚገኘው የሚዲያ ቡድን ታሪካዊውን የሶፍ ዑመር ዋሻ ጎብኝቷል።
ከባሌ ተራሮች ተነስቶ ቁልቁል የሚወርደው የዌብ ወንዝ ሰፊውን መሬት አቋርጦ ተጉዞ፣ በምሥራቅ ባሌ ዳዌ ቃጨና ወረዳ ግዙፍ የኖራ ድንጋይ ቋጥኝ ሥር ሲደርስ ድንገት የራሱን የምድር ውስጥ ዓለም ፈልፍሎ ሌላ ጉዞ ይጀምራል። ስሙም ሶፍ ዑመር ዋሻ ይሰኛል።
ይህ ድንቅ ቅርስ በ2013 ዓ.ም በታተመው የመቶ ብር ኖት የኋላ ገጽ ላይ በምስል ተካትቶ በየኪሳችን ቢዞርም፣ በውስጡ ያቀፈው ሚስጥር ግን በአካል ቀርቦ ለሚያየው ብቻ የሚገለጥ ረቂቅ የተፈጥሮ ሥነ-ሕንፃ ነው።
ሶፍ ዑመር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ጊዜያዊ መዝገብ ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ታላቅ የተፈጥሮና የባህል መዳረሻ ነው።
በጂኦሎጂ ዕይታ የኖራ ድንጋዩ ዕድሜ እና አፈጣጠር ላይ ጥናቶች የተደረጉ ቢሆንም ሶፍ ዑመር ዋሻ ካለው ጥልቅ ሀብትና ድንቅ ተፈጥሮ አንፃር በበቂ እንዳልተጠና ይነገራል።
በዩኔስኮ የቅርስ ሰነድ ላይ እንደተገለፀው የዋሻው ሥርዓት በማዮሲን (Miocene) ዘመን ውስጥ የተፈጠረ ሲሆን በቀደመው ዘመን የዌብ ወንዝ አቅጣጫውን ቀይሮ የኖራ ድንጋዩን እየቦረቦረ የፈጠረው እንደሆነ ይታመናል።
ይህ የምድር ውስጥ ዋሻ የምድርን የዝግመተ ለውጥ ታሪክ፣ ቀደምት የአየር ንብረት ለውጦችን እና የዘመናት ባዮሎጂያዊ ቅሪቶችን በውስጡ አምቆ የያዘ ሕያው የምርምር ማህደር ነው።
ከአፍሪካ ግዙፍ ተፈጥሯዊ ዋሻዎች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ሥፍራ እስከ 20 ሜትር የሚረዝሙ ግዙፍ የኖራ ድንጋይ ምሰሶዎች፣ ልዩ ልዩ ቅርጽ ያላቸው ደጋፊ ቅስቶች እና በሰው እጅ ተለክተው የተቀረጹ የሚመስሉ ረዣዥም ጣሪያዎች አሉት። በተለይም ግዙፉ ማዕከላዊ አዳራሽና ከዋሻው መውጫ አጠገብ ሆኖ ቁልቁል የሚፈሰውን ወንዝ ማየት የሚቻልበት የተፈጥሮ ሰገነት የሥፍራውን ግርማ ሞገስ ቁልጭ አድርጎ ያሳያሉ።
ዋሻው በአጠቃላይ 15.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ከ40 በላይ ዋና ዋና መግቢያና መውጫ በሮች አሉት።
ይህንን የምድር ውስጥ መንገድ በእጅ ባትሪና በካርታ ታግዞ ለመጓዝ ሦስት ሰዓት ተኩል ገደማ የጨለማ ውስጥ ጉዞ ማድረግ ይጠበቃል። በዚህ ጉዞ ወቅት ወንዙ በዋሻው ውስጥ ሰባት ጊዜ የሚተጣጠፍ በመሆኑ ተጓዦች ወንዙን ሰባት ጊዜ ያቋርጣሉ።
አምስቱን በእግር እየተራመዱ ሲሻገሩ ሁለቱን ደግሞ በዋና ወይም በጠባቡ የድንጋይ ክፍተት ላይ ከእንጨት በተሠሩ ድልድዮች በመጠቀም ያልፋሉ። በዚያ ጽልመት ውስጥ የሚገኙት ሕያዋን ፍጥረታት የሌሊት ወፎች፣ ዓሦችና ሸርጣን መሰል የውኃ ውስጥ አካላት ሲሆኑ በአቅራቢያው ወንዞች አዞዎች ቢኖሩም ወደ ዋሻው ውስጥ ግን ፈጽሞ አለመግባታቸው ሌላው አስገራሚ የተፈጥሮና መንፈሳዊ ሚስጥር ነው።
ከጂኦሎጂያዊ ውበቱ ባሻገር ሶፍ ኡመር በዓለም ላይ ካሉ ታላላቅ የዕምነት ሥርዓት ከሚከወንባቸው ዋሻዎች አንዱ ነው።
በአካባቢው ትውፊት እና በዩኔስኮ የቅርስ ሰነድ መሠረት በ11ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሼክ ሶፍ ኡመር አህመድ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ዋሻውን መጠለያና የመንፈሳዊ ትምህርት ማዕከል ካደረጉት በኋላ የእስልምና ሃይማኖት አስተምሮና ትውፊት ዛሬም ድረስ ቀጥሏል። የዋሻው እያንዳንዱ ክፍል ለልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥርዓቶች የተመደቡ ሲሆን በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄደው የሙዳ እና ሌሎች ሀይማኖታዊ ስርአቶች ከሩቅና ከቅርብ የሚመጡ ጎብኚዎችን ይስባሉ።
ከአዲስ አበባ በ532 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በዚህ መዳረሻ ላይ በቅርቡ እየተከናወኑ ያሉ መጠነ ሠፊ የመሠረተ ልማትና የሎጆች ግንባታዎች የሶፍ ዑመር ዋሻን ይበልጥ የዓለም የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል።
