“ሰራዊቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማደራጀት ለሀገር ህልውና ወሳኝ ነው” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ በታሪኳ ያካበተችው ጠንካራ የመንግስት ተቋማዊ አቅም፣ ሀገሪቱ በውስጥ እና በውጭ ፈተናዎች ውስጥም ሳትበገር እንድትቀጥል እንዳስቻላት በዛሬ የምክር ቤት ማብራሪያ ላይ ገልጸዋል።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 14K

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያ የነጻነት አርማ በመሆኗ አፍሪካን የመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለባት አስታውሰዋል። የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ በቅድሚያ የዜጎችን አንድነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ማንኛውም የውስጥ ግጭት በውይይትና በህግ አግባብ ሊፈታ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊትን ግንባታ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ ሰራዊቱ ለሀገር ልዕልና የሚዋደቅ ብቁ ተቋም እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ሰራዊቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና በከፍተኛ የውጊያ ስልት ማደራጀት የሀገሪቱን ድንበር እና ህገ-መንግስታዊ ስርአት ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በቴክኖሎጂ የተደገፈ የደኅንነት መረብ በመዘርጋት ከማንኛውም ስጋት ሀገሪቱን መከላከል የሚያስችል ስልት እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው ለሰራዊቱ የሚከፈል ክፍያና ጥቅማጥቅም የዘመኑን ፍላጎት መሰረት አድርጎ እየተሻሻለ እንደሚገኝ አብራርተዋል። ይህ የዘመናዊነት ሂደት ሰራዊቱ በሀገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ የሚከሰቱ የጸጥታ ስጋቶችን በብቃት ለመመከት የሚያስችል ብቃት እንደሚሰጠው ተገልጿል።
