ኢትዮጵያ የወደብ አልባ ሀገራትን የአቪዬሽን ትስስር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች
ከዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ኮንፈረንስ ጎን ለጎን በተካሄደው የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) የልማት አጋሮች ውይይት ኢትዮጵያ የወደብ አልባ ታዳጊ ሀገራትን የአቪዬሽን ትስስር ለማሻሻልና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጣለች።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ

በውይይቱ የድርጅቱ ቀጣናዊ ቢሮዎች፣ አባል ሀገራት፣ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት፣ የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን፣ የዓለም ባንክ፣ የፋይናንስና የልማት ተቋማት፣ ለጋሽ ሀገራት፣ አየር መንገዶች፣ የአውሮፕላን ማረፊያ አስተዳዳሪዎችና የግል ባለሀብቶችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በመድረኩ አምባሳደር ቴዎድሮስ ግርማ ኢትዮጵያ ለውጥኑ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት በማረጋገጥ የወደብ አልባ ታዳጊ ሀገራትን የአቪዬሽን ተግዳሮቶች ለመፍታት ቀጣይነት ያለው ዓለም አቀፍ አጋርነት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ተሳታፊዎቹም በሂደት ላይ ያሉ ሥራዎችንና መሻሻሎችን የገመገሙ ሲሆን የልማት አጋርነትን ለማጠናከር፣ ሀብት ለማሰባሰብና የአቪዬሽን ተነሳሽነቶችን ለማሳደግ በሚያስችሉ የወደፊት ስትራቴጂዎች ላይ መክረዋል።
