ወደ ዋናው ይዘት ዝለል

ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች የባሌ ተራሮችን ድንቅ ሀብት ጎበኙ

ጉብኝቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት "በብዝኃነት የደመቀች፣ በምክክር የፀናች፣ ስልጡን ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን 21ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ነው።

ዜና ክፍል · · 2 ደቂቃ ንባብ · 4

“You are not in the mountains. The mountains are in you.”
“አንተ በተራሮቹ ውስጥ አይደለህም፤ ተራሮቹ በአንተ ውስጥ ናቸው እንጂ” ይህንን አባባል ለባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ህያው ምስክር አድርጎ የሰጠው የብሔራዊ ፓርኮች አባት ተብሎ የሚጠራው አሜሪካዊው ጆን ሙይር ነው።

ይህ ድንቅ አባባል፣ የባሌ ተራሮችን ግርማ ሞገስና መንፈስን የመማረክ ኃይል ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ​ይህንኑ የተፈጥሮ ድንቅ ትዕይንት ለዓለም ለማስተዋወቅ፣ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ በሚገኘው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና አካባቢው ሰፊ የመስክ ጉብኝት አድርገዋል።

ጉብኝቱ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በኦሮሚያ ክልል አዘጋጅነት “በብዝኃነት የደመቀች፣ በምክክር የፀናች፣ ስልጡን ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን 21ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ነው።

​ከአዲስ አበባ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውና 2,150 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ይህ ግዙፍ ፓርክ በጉብኝቱ ለተሳተፉ ባለሙያዎች ያልተነኩ የተፈጥሮ ፀጋዎቹን ገልጦ አሳይቷል።

ባለሙያዎቹ በቆይታቸው ከኢትዮጵያ አልፈው ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የሕይወት እስትንፋስ የሆኑ ታላላቅ ወንዞች መነሻ ምንጮችን ተመልክተዋል። ከዚህም ባሻገር በ4,377 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘውን የቱሉ ዲምቱን ቁንጮ፣ የሳኔቴ አምባን ልዩ ገጽታ እንዲሁም በዲንሾና በተለያዩ የፓርኩ ክፍሎች የሚገኙ እንደ ቀይ ቀበሮና የደጋ አጋዘን ያሉ ብርቅዬ የዱር እንስሳትን፣ ልዩ ልዩ አእዋፋትንና ዕድሜ ጠገብ ደኖችን በቅርበት ጎብኝተዋል።

​በአሁኑ ወቅት ባሌን መጎብኘት ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ ምቹ እየሆነ መጥቷል። በአካባቢው እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ የመንገድ መሠረተ ልማቶችና ደረጃቸውን የጠበቁ ሎጆች፣ ጎብኚዎች የባሌ ተራሮችን ተፈጥሯዊ ውበት አጣጥመው እስከ አስደናቂው የሶፍ ዑመር ዋሻ ድረስ በቀላሉ ተንቀሳቅሰው ለመመለስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ መሆኑም ተገልጿል።

​የሚዲያ ባለሙያዎቹ በጉብኝቱ ያገኙትን ተሞክሮ በመጠቀም የባሌን ያልታዩ የቱሪዝም ፀጋዎች በዘመናዊ የዲጂታልና መደበኛ የሚዲያ አማራጮች ለዓለም ለማስተዋወቅ በርካታ ሥራዎችን እያዘጋጁ ይገኛሉ።

ይህ ጥረት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን ከዘላቂ የቱሪዝም ልማት ጋር በማስተሳሰር ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተጀመረውን እንቅስቃሴ ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።

አጋራ

YouTube

አማEN