ወደ ዋናው ይዘት ዝለል

የሴት አሰልጣኞች አቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከ ቲም አፕ ካናዳ (TeamUp Canada) እና ጎ ኢኖቬሽን (Go Innovation) ጋር በመተባበር ለሴት አሰልጣኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጥቷል።

ዜና ክፍል · · 2 ደቂቃ ንባብ · 2

Beyond The Game: Coaching Impact በሚል መሪ ቃል የተሰናዳው ይህ ስልጠና፣ አሰልጣኞች ከሜዳ ላይ ተግባራት ባለፈ በወጣቶችና በማህበረሰቡ ሕይወት ላይ ሊያሳድሩት በሚገባ አዎንታዊ ተጽዕኖና ኃላፊነት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። በስልጠናው ላይ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ፣ የሴቶች ከፍተኛ ሊግ እንዲሁም የፕሮጀክት አሰልጣኞች እንዲሁም የቀድሞ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ የብሔራዊ ቡድኖች ጥንካሬ የሚመነጨው ከክለቦችና ከታዳጊዎች ልማት ስርዓት መሆኑን ጠቁመው በሀገር ውስጥ የሊግ መዋቅሮችና በክለቦች ደረጃ የሚሰሩ ስራዎች እንዲሁም የታዳጊ ቡድኖች ዝግጅት በዕቅድና በጥራት መመራት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

አሰልጣኞች በራሳቸውና በተጫዋቾቻቸው ላይ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣት ከሀገር ውስጥ ውድድሮች ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማሰብ ይገባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ሴቶች የተለያዩ ተጽዕኖዎችን በማለፍ በእግር ኳሱ ልቀው ለመታየት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል። የሰሜን አሜሪካ የሴቶች እግር ኳስ የደረሰበትን ከፍታ እንደ ተሞክሮ በማንሳትም የኢትዮጵያ ሴት አሰልጣኞች ትምህርት ሊወስዱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሴቶች እግር ኳስ ላይ የ25 ዓመታት ልምድ ያላቸውና በሰሜን አሜሪካ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ከፍተኛ ብቃት ያካበቱት እና ስልጠናውን የሰጡት ግራሃም ሮክስበርግ በአሰልጣኝነት ጉዞ ውስጥ የሚያጋጠሙ ውድቀቶችና ልምዶች ለስኬት መሰረት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በጋራ ተሞክሯቸውን ያካፈሉትን ባልደረቦቻቸውንም ያስተዋወቁ ሲሆን በስልጠናው ላይ የቀድሞ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋች ብራያን ኤርቫይን፣ አሰልጣኝ ታይሰን ሃንተር፣ በካናዳ በፕሮፌሽናል የሴቶች እግር ኳስ ሊግ የምትጫወትና ከ ቲም አፕ ጋር የምትሰራው ጀኔያ ሮበርትሰን፣ በዩጋንዳ ወጣት ተጫዋቾችን በማብቃት የሚታወቁት ሪቻርድ ኦሉፖት እንዲሁም ዮሐንስ አክሊሉ እና ወርቅነህ ጅማ ተሳትፈዋል።

አጋራ

YouTube

አማEN