የውጭ ህክምና ጉዞን ለማስቀረት የአከርካሪና የህጻናት ቀዶ ህክምና በክልሎች ሊስፋፋ ነው
ዜጎች የመገጣጠሚያ ቅየራ፣ የጀርባ አከርካሪና ከባድ የህጻናት አጥንት ህክምናን ለማግኘት ወደ ውጭ ሀገር የሚያደርጉትን ጉዞ ለማስቀረት ንዑስ ስፔሻሊቲ ስልጠናዎችን በሀገር ውስጥ እያስፋፋ መሆኑን የኢትዮጵያ የአጥንት ቀዶ ህክምና ማህበር አስታወቀ።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 1

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኤፍሬም ገብረሃና በ19ኛው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ እንደገለጹት ዘንድሮ ስድስት ባለሙያዎችን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት 13 ሐኪሞች በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ በውጭ ሀገራት ንዑስ ስፔሻሊቲ ተምረዋል።
በሀገር ውስጥም በኪዩር ኢትዮጵያና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታሎች የተጀመሩት የህጻናትና የከፍተኛ አደጋ ስልጠናዎች በቀጣይ ዓመት አከርካሪን ጨምሮ በሶስት ዘርፎች በተለያዩ ክልሎች እንዲሰጡ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ይሁንና የአጥንት ህክምና መሳሪያዎች በሰውነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩና ብዙ ባዮሎጂካል ምርመራዎችን ማለፍ ያለባቸው በመሆናቸው ሀገር ውስጥ የማምረት አቅም ባለመፈጠሩ ከውጭ መምጣታቸው ህክምናውን ውድ እንዳደረገው የስራ አስፈጻሚ አባሉ ዶ/ር መንግስቱ አብራርተዋል።
ከ132 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ባለባት ሀገር 790 የደረሰው የማህበሩ አባላት ቁጥርም ገና በቂ አለመሆኑንና ወደ ወጌሻ መሄድን ለማስቀረት ግንዛቤ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በተዘጋጀውና 23 ተቋማት የቀዶ ህክምና የኤክስሬይ መሳሪያዎችን ጨምሮ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ባቀረቡበት በዚህ ጉባኤ ዶ/ር ቴዎድሮስ ጥላሁን ከመኪና፣ ግንባታና ግጭት የሚመነጩ ጉዳቶችን አሳሳቢነት አንስተዋል።
በማጠቃለያም በየዓመቱ ከሶስት ሺህ በላይ ህጻናትን በነጻ ለሚያክመው ኪዩር ኢትዮጵያ ሆስፒታል፣ በደሴ ለ35 ዓመታት ላገለገሉት ዶ/ር ዘላለም ተአምራትና ለዶ/ር ማንያዘዋል ደሴ ሽልማት ተበርክቷል።
