የገቢዎች ቢሮ ሰራተኛ ነን በማለት ሲያጭበረብሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች በመምሰል በንግድ ተቋማት ላይ ማጭበርበር ሲፈጽሙ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 3

ተጠርጣሪዎቹ በቱሉ ዲምቱ ወረዳ በሚገኙ የንግድ ቤቶች እየዞሩ ያለ ደረሰኝ ግብይት ፈጽማችኋል በሚል ሰበብ ከ100 ሺህ ብር ቅጣት አድናችኋለን በማለት 50 ሺህ ብር ጉቦ ሲጠይቁ እንደነበር ተገልጿል።
ግለሰቦቹ የሐሰት መታወቂያዎችን በመጠቀም በሌላ ስም ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ሲሆን በንግዱ ማህበረሰብ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም የገቢዎች ቢሮ እና የመሬት ባለሙያ መሆናቸውን የሚያሳዩ የሐሰት መታወቂያዎች ተገኝተውባቸዋል።
የቢሮው የሕግ ተገዢነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፓርቲ ንጉሴ የገቢዎች ቢሮ ሰራተኞች ባርኮድ ያለው መታወቂያ እንደሚጠቀሙ ገልጸው ግብር ከፋዮች የባርኮድ ስካን በማድረግ የሰራተኞችን ማንነት እንዲያረጋግጡ አስገንዝበዋል። ተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝም ተገልጿል።
