12 ሀገራት የሚካፈሉበት የአፍሪካ መስማት የተሳናችው እግር ኳስ ውድድር ሰኞ በአዲስ አበባ ይጀምራል
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው እግር ኳስ ማህበር ከአፍሪካ መስማት ከተሳናቸው ማህበር ጋር በመተባበር 12 ሀገራት የሚሳተፉበት የአፍሪካ መስማት የተሳናቸው እግር ኳስ ሻምፒዮና ውድድር በቀጣይ ሰኞ ህዳር 21 እንደሚካሄድ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አሳውቋል።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 1

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ውድድር ታስተናግዳለች፣ በቀጣይ ሌሎች ሀገራት ያስቀጥላሉ ብለን እናስባለን ያሉት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ድኤታ አቶ መኪዩ መሀመድ
በስፖርቱ በሁሉም ዘርፍ መሳተፍ ከቻልን ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ብለዋል።
እንደባለፈው አመቱ ሁሉ አዲስ አበባ ከተማ በአትሌቲክሱ ፣ በተለያዩ ኮንፈረስ እንዲሁም ሌሎች የስፖርት ውድድሮች በዓመቱ ከተማዋ እንደምታስተናግድ የገለፁት አቶ መኪዩ በስፖርቱ አካታች መሆን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ሁለት ስራዎችን ማለትም ማዘጋጀትና መሳተፍ አላማ አድርገን እንደ ፌዴሬሽን እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉ ሲሆን 20 ኢትዮጵያውያን ዳኞች ጨዋታው ይመራሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያን የሚወክሉ መስማት የተሳናቸው እግር ኳስ ተጫዋች ሆቴል ተሰባስበው ልምምድ እየሰሩ የሚገኙ ሲሆን ወጪዎችን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እየሸፈነ እንደሚገኝ አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል ።
ውድድሩ በአዲስ አበባ ስታዲየም እና በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል።
