ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ከፕሬዝዳንት ኤርዶሀን ጋር ተወያዩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በCOP31 የመሪዎች ጉባኤ ዋዜማ በአንታሊያ ተርኪዬ በመገኘት ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶሀን ጋር ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን አስታወቁ።
ዜና ክፍል · · 1 ደቂቃ ንባብ · 3

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በCOP31 የመሪዎች ጉባኤ ዋዜማ በአንታሊያ ተርኪዬ በመገኘት ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይብ ኤርዶሀን ጋር ፍሬያማ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፤ዘ ውይይታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነት መሠረት በማድረግ፣ የሁለትዮሽ ትብብርን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ዕድሎች ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ተርኪዬ COP31ን ለማስተናገድ ላደረገችው ዝግጅት እና ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ እያሳየች ላለው ጥረት አድናቆታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህም ኢትዮጵያ የCOP32 ፕሬዝዳንትነትን ለመረከብ በምታደርገው ዝግጅት ላይ ጠንካራ አጋርነት እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
መሪዎቹ በጋራ ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ባላቸው ዕድሎች ላይ የመከሩ ሲሆን በጋራ ቅድሚያ በሚሰጧቸው መስኮች ላይ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ እና ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
