በኢትዮጵያ ያልታሰበ የወጣት ሴቶች እርግዝና 13 በመቶ እንደደረሰ ጥናቶች ያመለክታሉ ። ምንም እንኳን በመንግስት በኩል ይህን ቁጥር ለመቀነስ የሚደረገው ርብርብ አበረታች ቢሆንም ይህን ቁጥር ለመቀነስ ከመንግስት ድርጅቶች በተጨማሪ የግሉን ዘርፍ እምቅ አቅም በመጠቀም ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ተደራሽነትን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ይህን በማስመልከት ሀንዝ የማማከር አገልግሎት ከጤና ሚኒስተር ጋር በመተባበር ለ አንድ ዓመት ያክል ትግራይና አፋርን ሳይጨምር በሁሉም ክልሎች ያደረገውን ጥናት ዛሬ ይፋ አድርጓል ።
በጥናቱ የተገኙት የጤና ሚኒስተር የ እናቶች የህጻናትና የወጣቶች ጤናና የስርዐተ-ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በሀገሪቱ የእርግዝና መከላከያ መንገዶችን የሚጠቀሙ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ቢሄድም ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር ይበልጥ ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የጥናቱ መሪ የነበሩት አቶ ዘላለም አዱኛ በበኩላቸው መንግስት ብቻውን ሲሰራቸው የቆያቸው ስራዎች ብቻ በቂ ባለመሆናቸው ዘመን ያፈራቸውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሌሎች አካላትን በማከተት ተደራሽነትን ማስፋት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ቆየት ያሉ አሰራሮችን በመቀየር አገልግሎቱን ለሚፈልጉ ሁሉ ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-10-28
