በአዲስ አበባ 5 ሺሕ ተገጣጣሚ ቤቶች ሊገነቡ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ የመዲናዋን የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል በሚል የአቃቂ ተገጣጣሚ ቤቶች ፕሮጀክትን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ በከተማዋ ከዓመታት በፊት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች የሚሆኑ መሰል የተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታን ለማካሄድ ቢያቅድም ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል፡፡ መዲናዋ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት ያለባት ከተማ ስትሆን በ2005 በተደረገው የጋራ መኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከ900 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ እስካሁን ቤቶቹን አላገኙም። የአቃቂ ተገጣጣሚ ቤቶች በ1 ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቁ ሲሆን ግንባታው የሚካሄድበት ቦታ ከዚህ ቀደም በሕገ ወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ መሆኑን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡ ግንባታውን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ያከናውነዋል መባሉም ተነግሯል።
በሀገሬ ቲቪ
2022-01-12
