ሀገሬ ቲቪ

በአበባ አምራች ተቋም የሚሠሩ ሠራተኞችን መብት የሚያስከብር ፕሮግራም ይፋ ሆነ

በጎርጎሮሲያኑ 2005 የተቋቋመው ፌርትሬድ አፍሪካ የተሰኘው ግብረሰናይ ድርጅት በዋናነት በአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለያዩ የግብርና ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ገበሬዎች፣ ማኀበራትና ተቋማት ድጋፍ ያደርጋል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ደግሞ በቡና እና የአበባ ምርት ላይ ለተሰማሩ አካላት የተለያዩ ድጋፎችን ይሰጣል። በዛሬው ዕለትም ታዲያ ዶናትስ የተሰኘ እና ለአራት ዓመት የሚቆይ አዲስ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል።

አበባ በሚያመርቱ ተቋማት ያሉ ሰራተኞች መብት የተጠበቀ እንዲሆን እና በቡና ገበያው አስተማማኝ የንግድ ሰንሰለት እንዲኖር እንደሚደረግ የፌርትሬድ አፍሪካ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ቀጠና ኃላፊ ኃላፊ ካስፖር ፔዶ ተናግረዋል።

የዶናትስ ፕሮጀክት በ7 የአበባ እርሻ ተቋማት ላይ የሚተገበር ሲኾን በዋናነት 16 ሺህ ሰራተኞ ባሉት እና ሼር ኢትዮጵያ በሚባለው ተቋም ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ የፕሮግራሙ አስተባባሪ የኾኑት አቶ ዳንኤል ቤሌማ ነግረውናል።

ሰራተኞች መብታቸውን ማስከበር በሚችሉበት መንገድ ላይ ድጋፍ ይደረጋል።

ፌርትሬድ አፍሪካ ሌላው ይፋ ያደረገው ፕሮግራም በሲዳማ ይርጋጨፌ እና በቤንቺማቺ አካባቢዎች አነስተኛ ቡና አምራች አርሶአደሮች በማኀበራቸው ዘላቂ የገበያ ትሥሥር እንዲኖራቸው እንዲሁም የአካታችነትን ሥራ እንዲኖር የሚረዳ መኾኑን የፕሮግራሙ አስተባባሪ የኾኑት አቶ ዳንዓኤል ቤሌማ ነግረውናል።

ፌርትሬድ አፍሪካ ዛሬ ይፋ ያደረገው ዶናትስ የተሰኘው ፕሮግራም በአጠቃላይ ከ 1 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በጀት ተይዞለታል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-10-31