ሀገሬ ቲቪ

አስገራሚው የኮቪድ19 መከላከያ ክትባት

ክትባት ስንል ወደ አዕምሯችን ከሚመጣው መርፌ ለየት ያለ ክትባት ከወደ ቻይና ለዜጎች እየተሰጠ መሆኑን ሰማን እና ልናጋራችሁ ወደድን።

በሻንጋይ ይህን በአይነቱ ለየት ያለ የኮቪድ 19 ክትባት ለመውሰድ ነዋሪዎች ተሰልፈዋል ። ተራ የደረሰው ሰው ፊርማውን በማኖር ከህክምና ባለሞያዋ በአንዲት ኩባያ የተሰጠውን መድሀኒት ወደአፉ በማስጠጋት ወደ ውስጥ ይስበዋል።

ጨረሰ ይህ ሰው ምንም አይነት መርፌ ሳይወጋ የኮቪድ 19 ቫይረስን የሚታገል ክትባት ወስዷል ማለት ነው ።

ይህ ክትባት ኤርሶል የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን ከጥቅምት 25 ጀመሮ በአንዳንድ የቻይና አካባቢዎች መሰጠት መጀመሩን ሰምተናል ።

በቀጣይም ሁሉም ቻይናዊ እንዲወስደው እየተሰራ ነው ተብሏል ። ክትባቱን ወስዶ እንዴት ነበር ተብሎ የተጠየቀ አንድ ግለሰብም እንዲ ሲል መልሷል ።

“በኩባያ ወተት ወይም ሻይ የምጠጣ ነው የመሰለኝ ። ደግሞ ጣፋጭ ነው ።”

የሳይንስ ተመራማሪዎች ይህ ክትባት መርፌን በማስቀረቱ እንዲሁም በቀላሉ ሊሰጥ በመቻሉ ስለክትባት ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ የሆኑ አገሮች በቀላሉ ሊወስዱትና የተከታቢውን ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብለዋል ።

የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ መዕከል ባለስልጣን የሆኑት ዡ ጂ በበኩላቸው የክትባቱን ጠቃሚነት ገልጸው ነገር ግን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊጠቀመው አይችልም ብለዋል ።

“ክትባቱ ለሁሉም ሰው የሚሆን አይደለም ለምሳሌ እንደ አስም እና ሌሎች የመተንፈሻ አካላት በሽታ ያለባቸው፣ ሥር የሰደደ የሳንባ በሽታ ተጠቂ የሆኑ ሰወች ይህ ክትባት ላይስማማቸው ስለሚችል እንዲወስዱት አይመከርም ።”

ታዲያ ይህን አጃኢብ ያሰኘ ክትባት ባለሞያው ባይወስዱት ይመከራል ካሏቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በስተቀር እድሜያቸው ከ 18 ዓመት በላይ የሆኑ ሁሉ መውሰድ ይችላል ተብሏል ።

በሳምሶን ገድሉ
2022-11-01