ሀገሬ ቲቪ

የአዲስ አበባ የትምሕርት ስርዓት አተገባበር በርካታ ችግሮች አሉበት ተባለ

የአዲስ አበባ የትምህርት ስርዓት አተገባበር በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ተገለጸ። በከተማዋ አንድ የትምህርት ፖሊሲ ቢኖርም ከአተገባበር አንጻር አራት ዓይነት ትምህርት ቤቶች ተፈጥረዋል ተብሏል።

በሀገራችን አዲስ ስርዓተ ትምህርት መቀረጹን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ በማጥናት ወደ ትግበራ መግባቱን አስታውቋል።

የከተማዋ የስርዓተ ትምህርት አተገባበር ላይ የአዲስ አበባ ት/ቢሮ ከትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር ባዘጋጁት ውይይት በከተማዋ የት/ት ስርዓት አተገባበሩ በርካታ ችግሮች አሉበት ተብሏል።

የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ም/ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፍቅርተ አበራ በከተማዋ አንድ የትምህርት ፖሊሲ ቢኖርም ከአተገባበር አንጻር አራት ዓይነት ትምህርት ቤቶች ተፈጥረዋል ብለዋል።

ወ/ሮ ፍቅርተ በከተማዋ ባሉ የግል ትምህርት ቤቶች የሌሎች ሀገራት የትምህርት ስርዓትን ገልብጦ መጠቀምን ብሎም በአፍ መፍቻ ቋናቋ ሳይሆን በእንግሊዘኛ ብቻ ማስተማርን የጥራት መለኪያ አድርጎ የመመልከት ችግር እንዳለ ጠቁመዋል።

ለ26 ትምህርት ቤቶችም የስርዓተ ትምህርት ጥሰት ጋር በተያያዘ የታረሙ ደብዳቤ ተልኳል የተባለ ሲሆን የቁጥጥር ስራው ይቀጥላል ተብሏል።

የአዲስ አበባ ት/ቤሮ ም/ኃላፊ አቶ አድማሱ ደቻሳ አዲሱ ስርዓተ ትምህርትን በከተማዋ ከመተግበር አንጻር ነባሩን የትምህርት መጽሃፍ የመጠቀም አዝማሚያ ስለመኖሩ ተናግረዋል።

በአዲሱ የትምህርት ስርዓት መሰረት ለከተማዋ 3.9 ሚሊዮን መጻህፍት ለህትመት ቢታዘዙም ማሰራጨት የተቻለው 1.2 ሚሊዮን ያክሉ ብቻ ነው ያሉ ሲሆን በሶፍት ኮፒ ለጊዜው እንዲገለገሉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የህትመት ስራው በዚህ ወር መጨረሻ እንዲጠናቀቅም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-11-01