ሀገሬ ቲቪ

ዓለም አቀፍ ትኩረት የኾነው የሰላም ስምምነት

በደቡብ አፍሪካ የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ተወካዮች ከሳምንት በላይ ሲካሔድ የቆየው የሰላም ንግግር በስምምነት መጠናቀቁ ይፋ ኾኗል።

በትላንትናው ዕለት ይፋ በኾነው ሥምምነት ኹለቱም ተደራዳሪዎች ዝርዝር የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

በዚህ መግለጫ በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ተስማምተዋል።

ኢትዮጵያ አንድ መከላከያ ሠራዊት ብቻ እንዳላት እውቅና በመስጠት ህወሓት መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ባስገባ ሁኔታ ትጥቅ እንዲፈታ እና ሁሉንም የቡድን እና ከባድ መሣሪያዎች ለመከላከያ ሠራዊት እንዲያስረክብ ተስማምተዋል።

የሁለቱ አካላት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ይህን ተፈጻሚ በማድረጉ ጉዳይ ላይ በፍጥነት ውይይት ይጀምራሉም ተብሏል።

የትግራይን ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ቀድሞ ወደነበረበት መመለስና የሽግግር እርምጃዎችን ተግባራዊ ማድረግ ሌላው የስምምነቱ አካል ነው።

የጥላቻና የፕሮፖጋንዳ ንግግሮችን ጨምሮ ግልጽ እና ስውር የግጭት ድርጊቶችን ማቆም፤ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንዲሁም የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የፌደራል መንግሥት በሰላማዊ እና በተቀናጀ መንገድ መቀሌ እንዲገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ይህ ከኾነ በኋላ አሁን ያለውን አስተዳደር የሚተካ የፌደራል መንግሥት የሚመራው የጊዜያዊ አስተዳደር የሚቋቋም ሲኾን በሚዋቀረው ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥም የትግራይን ሕዝብ የሚወክል አካል እንደሚሳተፍ ተሰምቷል።

ሌላው ስምምነቱ ተግባራዊ የሚያደርጋቸው ጉዳዮች መካከል በሕዝብተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጆ የነበረው ህወሓት ከአሸባሪነት መዝገብ ለመፋቅ፤ በሕወሃት ተዋጊዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ ለማቆም፣ የፌደራል መንግሥቱ መስማማቱን በዚሁ የጋራ መግለጫ ተካቷል።

ይህን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ወሳኝ እርምጃ ነው ሲሉ ስምምነቱን አድንቀዋል።

አሜሪካ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲኾን ድጋፌን አደርጋለሁ ስትል በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃለች የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ፖሊሲ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬ ስምምነቱን አድንቀወ መሠረታዊ አገልግሎቶች ማስጀመር ቅድሚያ እንዲሰጠው ጠይቀዋል ኬኒያም ቢኾን የኢትዮጵያን የሰላም ጉዞ ለመደገፍ ቁርጠኛ ነኝ ብላለች።

በሙሉጌታ በላይ
2022-11-03