ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በደቡብ አፍሪካ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ እንዳሸነፈች ነው የገልጹት።
ጠቅላይ ሚንስትሩበትላንትናው ዕለት በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በማስመልከት በጋሞጎፋ ዞን ባስተላለፉት መልዕክት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት በርካታ መሰናክሎች እና ጣልቃ ገብነቶች የነበሩበት እንደነበር ጠቁመዋል።
በተደረሰው የሰላም ስምምነት ሁለቱም አካላት የሀገርን ሊዓላዊነት ለድርድር የሚቀርብ አለመሆኑን መተማመናቸውን አንስተዋል።
ያለፉ ትላንቶቻችንን ወደ ኋላ ተወት አድርገን በይቅር ባይነት መንፈስ ወደ ፊት መነሳት እንደሚገባ ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ የአስተዳደር ወሰንን በሚመለከት ደጋግመው ለሚነሱ ጥያቄዎችም በሰላማዊ መንገድ በመመካከር ብቻ መፍትሄ እንደሚሰጠውም ተናግረዋል።
አላስፈላጊ መስዋዕትነትን ያስከፈለ ነው ባሉት በዚሁ ጦርነት ጉዳት ለደረሰበት የትግራይ ህዝብ ድጋፍ ለማድረግ እና አንድነታችንን ለማሳየት ኢትዮጵያውያን በጋራ ልንነሳ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ካሳለፍናቸው ነገሮች ልንማር እንደሚገባ ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ልዩነት ያላችሁ ሁሉ ልዩነቶቻችን ላይ በመመካከር የተሻለች ኢትዮጵያን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም ለሀገር ሉዓላዊነት መስዋዕት ለሆኑ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-11-03
