ለወትሮ ሀገር ጀግናዋን አጣች ሲባል በአዕምሮዎ ቶሎ ብቅ የሚለው ምንድነው? እርሶ የፈለጉትን ያስቡ ካምቦዲያ ግን ጀግናዬ ነው ያለችውን ማጋዋ በሚል ስያሜ የሚጠራውን አይጥ አጥታለች። ሟች አይጥ በሀገሪቱ የተቀበሩ ፈንጂዎችን እያነፈነፈ አድራሻቸውን የሚጠቁም ሳተና ነበር ነው የተባለው። የተቀበረ ፈንጂን ካለበት አሽቶ ይመክን ዘንድ ሲለፋ የነበረው አይጥ በድንገት ህይወቱ ማለፉን አልጄዚራ አስነብቧል። ማጋዋ ከአፍሪካ ምድር የተገኙ አይጦችን ፍንጂ ያምክኑ ዘንድ በሚያሰለጥናቸው መቀመጫውን ቤልጄም ባደረገው አፖፖ በተሰኘው ተቋም ፈንጂ የማምከን ጥበብን ተምሯል። አይጡ ፈንጂ በማምከን ባሳለፋቸው አምስት ዓመታት ውስጥ ከ100 በላይ ፈንጂዎችን እንዲመክኑ ማድረግ የቻለ የካምቦዲያ ባለውለታ ነው። ታዲያ በነዚህ ዓመታት ውስጥ ላበረከተው የማይተካ አስተዋጻኦ ከሀገሬው መንግስት የጀግንነት ሜዳልያን አጥልቋል። ለአስር ዓመታት በቆየው የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ስትታመስ በቆየችው ሀገር ካምቦዲያ 386 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን መሬት አሁንም በውስጡ አውዳሚ ፈንጂዎችን ታቅፎ ይገኛል። ታዲያ የማጋዋ ውለታ በካምቦዲያ ውስጥ ያሉ ማህበረሰቦች ህይወት ወይም አካል ማጣትን ሳይፈሩ እንዲኖሩ እና እንዲሰሩ ያስቻለ ነውም ተብሎለታል። ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ጡረታ የወጣው ማጋዋ ከተወለደ በስምንት ዓመቱ መልካም በዋለላት ካምቦዲያ ውስጥ ህይወቱ አልፏል።
በሀገሬ ቲቪ
2022-01-12
