ምልዐተ ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ዕድገት ለሀገሪቱ ማህበራዊና ልማታዊ ክንውን እንዲሁም ለመላው ሕዝቦች ሰላምና አንድነት ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ውሳኔውን አስመልክቶ መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በቅዱስ ሲኖዶሱ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና ቀን ከለሊት ፀሎት ሲጸለይበት የነበረው የሰሜኑ ጦርነት የሰላም ስምምነት ላይ በመድረሱ ሲኖዶሱ መደሰቱን ገልጸዋል። ሁሉም አካል ሰላሙ ፍጻሜ እንዲያገኝ በትኩረት መስራት አለበት ብለዋል ።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል እንዲሁም በውጪ ያሉ አንዳንድ አብያተ ክርስትያናት እያሳዩት ያለውን ያልተገባ አኪያሄድ እንዲያርሙም ሲኖዶሱ ጥሪ አቅርቧል ።
በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙት የኪልቅያ ሊባኖስ መንበር የሆኑ ሶስት አብያተ ክርስትያናት በሀገረ ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ገዳም ይዞታን አስመልክቶ የሰጡት አሳዛኝ መግለጫ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በትኩረት መመልከቱን ገልጸዋል ።
በመጨረሻም በሰሜኑ ክፍል በተቀሰቀሰው ግጭት ተጎጂ የነበሩ ዜጎችን ሀይማኖት እና ብሄር ሳይለዩ ሲያጽናኑ ፤ እንዳይራቡና እንዳይጠሙ ያላቸውን በመደገፍ ከጎናቸው ለቆሙ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ራሳቸውን በትምህርት በመደገፍ ለቤተክርስቲያኗ እድገት የበኩላቸውን ለተወጡ አባቶች ሲኖዶሱ የምስጋናና የምስክር ወረቀት አበርክቶላቸዋል ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-11-04
