የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ዕውቀታችን ደካማ መሆን ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑን አሉታዊ ዓላማ ያላቸው ቡድኖች እና ግለሰቦች እንዲጠቀሙበት ምክንያት መሆኑ ተጠቆመ። የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም እውቀታችንን ማሳደግ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
የማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃን ከጊዜ ወደ ጊዜ ብዙ ተጠቃሚዎችን በተለይም ወጣቶችን በመሳብ ላይ ያሉ የመረጃ መለዋወጫ መንገዶች ናቸው።
እነዚህን የማህበራዊ ትስስር አማራጮችን በጥንቃቄ መጠቀም እንደሚገባ ደግሞ በዘርፉ ላይ ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎች ያሳስባሉ።
በሀገራችን ያለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዕውቀት ደካማ መሆን አሉታዊ ዓላማ ላላቸው ቡድኖች መጠቀሚያ እንዲሆንም ምክንያት መሆኑን የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ፕሮግራም ኃላፊ አጥናፉ ብርሃኔ ገልጸውልናል።
በሀገራችን የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ ላይ የሚሰራጩ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች በተደጋጋሚ ካጋጠሙን ግጭቶች ጋር የተመጋጋቢነት ትስስር እንዳላቸው የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር በሱፍቃድ ኃይሉ ባደረገናቸው የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ዳሰሳዎች ለይተናል ብለውናል።
በቅርብ ጊዜ በሀገራችን የተከሰቱ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ፖለቲካዊ ፍላጎት ካላቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች በተጨማሪ ባለማወቅ የተዛቡ መረጃዎችን የሚያጋሩ እና የጥላቻ ንግግሮችን የሚያስፋፉ መኖራቸው ግጭቶቹን እንዲባባሱ እንዳደረጓቸው የጠቀሱት አቶ በሱፍቃድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው ግጭቶችን የሚያባባሱ የተዛቡ መረጃዎችን እና የጥላቻ ንግግሮችን በመለየት በኩል የራሱን ጥንቃቄ መውሰድ እንደሚኖርበት ጠቁመውናል።
የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ፕሮግራም ኃላፊ አጥናፉ ብርሃኔ ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚውን የዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀም ዕውቀት እና ክህሎት በማዳበር በኩልም ተቋማት ሊሰሩ እንደሚገባቸው ነግረውናል።
እስከዛሬ በተዛቡ እና በተሳሳቱ መረጃዎች ብሎም የጥላቻ ንግግሮች የከፋ ጉዳት እንዳደረሱት ግጭቶች ሁሉ መሰል ተግባራት እንዳይደገሙ ለማድረግ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃኑ የሚጋሩ የተዛቡ እና የተሳሳቱ ብሎም የጥላቻ ንግግሮችን ዝም ልንላቸው እንደማይገባም ጠቁመውናል።
በአብርሃም በለጠ
2022-11-04
