የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዛሬ ጥቅምት 28/2015 ዓ.ም ሊተገብራቸው ያሰባቸውን የሶሥት ዓመት ቀጣይ ዕቅዱን ይፋ አድርጓል።
ከዚህ ቀደም በሀገር አቀፍ ደረጃ በአውሮፓውያኑ 2030 ወይም ከስምንት ዓመት በኋላ በሀገሪቱ ሁሉም ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንዲኾኑ ወጥኜ ቢኾንም አሁን ባለው አካሔዴ ይህን ለመፈጸም አልችልም ብሏል።
ስለዚህም ይህን እቅድ ለመከለስ መገደዱን የተቋሙ የለውጠና መልካም አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ እሱባለው ጤናው ተናግረዋል።
የፋይናንስ እና የግብዓት ዕጥረት ደግም ዕቅዱ በታሰበው ልክ እንዳይጓዝ ተግዳሮት እንደኾነ አቶ እሱባለው ገልጸዋል።
እንደተግዳሮት የተነሱት በተለይም የፋይናንስ ዕጥረቱ በመንግሥትም ኾነ በአበዳሪ ተቋማት የሚቀረፍ ከኾነ ግን ሁሉንም ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የማድረጉ ዕቅድ በተያዘለት ዓመት መሳካት እንደሚችል የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የኾኑት አቶ ሽፈራው ተሊላ ናቸው።
በዘንድሮ በጀት ዓመት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አባወራዎች ቁጥር አሁን ካለበት 4.3 ሚሊዮን ወደ አምስት ሚሊዮን ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል።
የሶስት ዓመቱ ዕቅድ በሚጠናቀቅበት በ2017 ዓ.ም ደግሞ ይህ ቁጥር ወደ 22 ሚሊዮን ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሌላው በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የኤሌክትሪክ መሠረተልማቶች ዝርፊያእና ውድመት ተቋሙን በከፍተኛ ሁኔታ እየፈተኑት ነው ተብሏል።
የአልሙኒየም ብረቶችን ከሚዘርፉ ግለሰቦች የሚረከቡ ኢንዱስትሪና ባለሀብቶች መኖራቸው ደግሞ ችግሩን የጎላ እንዳደረገው አቶ ሽፈራው ተሊላ አስረድተዋል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-11-07
