ሀገሬ ቲቪ

በሞላ ግድብ ላይ የሚያንሸራሽረው ባቡር

ችግር መላን ይወልዳል፤ የወንዛችን አባባል ነው። ታዲያ በታይላንድም እንዲሁ ነው የሆነው። ታይላንድ ከሳምንታት በፊት እንዲህ እንዳሁኑ አልነበረችም።

ጥሎ የነበረው ከባድ ዝናብ ባሲያ ሀገሪቷን ጎርፍ ውጧት ቆይታለች። ታዲያ ይህ መከረኛ ጎርፍ የሀገሪቱ የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ቀላል የማይባል ጉዳትን አስከትሎም ነበር።

የሀገሬው የባቡር ማጓጓዣ ኃላፊዎች እጅ እና እግራቸው አጣጥፈው አልተቀመጡም። ደጋግሞ በሚፈትናቸው በዚያ ከባድ ዝናብ ላይ ሀገራቸውን ደገፍ የሚያደርጉበትን መላ ከዘየዱ ዓመታትን ተሻግረዋል።

የሚያስተዳድሩት ባቡር አቋርጦት የሚያልፈውን በውሃ የተሞላ ግድብ ለተሳፋሪዎች እየተጓዙ እንዲዝናኑበት ማድረግ።

ይህ ግድብ ከሳምንታት በፊት ጥሎ በነበረው ዝናብ ሳቢያ ከአፍ እስከገደፉ ጢም ብሎ የሞላ ነው። ስሙም ፓሳክ ጆልሲድ ግድብ ይሰኛል።

ላመል ያህል በተፈፈችው የመጓጓዣ ቦታ ላይ በተዘረግው ሃዲድ እየተጓዘ ባቡሩ ሰዎችን በሃሴት እየሞላ ይገኛል። ጉዞው ከሀገሪቱ ርዕሰ መዲና ባንኮክ ይነሳና ፓሳክ ጆልሲድ ግድብ አቋርጦ የሚያልፍ ነው።

ታዲያ በአንድ ሰንበት ብቻ (ባሳለፍነው እሁድ) 600 ተጓዦች በባቡር ተሳፍረው በዚህ ግድብ መሀል ላይ ፎቶዎችን ሲነሱ እና ሲዝናኑ ተስተውለዋል።

በሀገሪቱ ባለው በዚሁ ግዙፍ ግድብ ላይ ከሚዝናኑት መሀከል አንድ ተጓዥ የተሰማውን እንዲህ አጋርቷል።

“በዚህ በሚንሳፈፈው ባቡር ላይ ለመሳፈር ከፈለኩኝ ዓመት አልፎኛል፤ ትኬቶቹ ሁሉ ተሽጠው በማለቃቸው ሳቢያ እስከዛሬ ሳልሳፈር ቆይቻለው። በዚህ ዓመት ግን ገና የታይላንድ የባቡር ባለስልጣን ትኬት መሸጥ መጀመሩን ይፋ እንዳደረገ ነው ተሽቀዳድሜ የገዛሁት። እይታው በጣም ይማርካል። በጣም ተደስቻለው። ይህንን በማየቴ በጣም እድለኛ ነኝ።”

ተጓዦቹ በዚህ ግድብ ለማቋራጥ ከመዝናኛ ሰዓታቸው ጋር ተደምሮ ስድስት ሰዓታትን ይወስድባቸዋል።

ባለንበት ዓመት የውሃው መጠን በእጅጉ ጨምሮ መመዝገቡ በውሃው ላይ ለሚጓዙ ሰዎች የተለየ ድባብን እንዳላቸሰው ተጠቁሟል።

የዚህ ባቡር በግድብ ላይ የመንሳፈፍ እና ሰዎችን የማዝናናት ጉዞው የሚደረገው በእረፍት ቀናት ብቻ ነውም ተብሏል።

ቀሪውን የሳምንቱ ቀናት ባቡሩ እረፍት ያደርግባቸዋል። ታዲያ ሌላኛው አስገራሚው ነገር ደግሞ በዚህ ባቡር ለመሳፈር ልባቸው የሻተ ካሉ ሌላ ቀጣይ ዓመትን መጠበቃቸው ነው።

እስከ ፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ድረስ የዚህ ባቡር ሁሉም ወንበሮች ገንዘብ የተከፈለባቸው ናቸው።

በሳምሶን ገድሉ
2022-11-08