የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ከታክስ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች ላይ የይግባኝ ውሳኔ እየሰጠ ቢሆንም ብዙ ተገልጋዮች ስለኮሚሽኑ ዕውቅና የላቸውም ተባለ። ኮሚሽኑ የ2015 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት አፈጻጸሙ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
እንደኮሚሽን ተቋቁሞ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ታክስ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች ላይ የይግባኝ ውሳኔ የመስጠት አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም ብዙ ተገልጋዮች ስለኮሚሽኑ ዕውቅና የላቸውም ሲሉ የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ አያሌው ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የ2015 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸሙን ለጋዜጠኞች ባቀረበበት ከቀረቡለት የ1.4 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 501 የቅሬታ መዛግብት 202 ያክሉን ለውሳኔ ቀጥሮ ለ202ቱም ውሳኔ መስጠት መቻሉን ያስታወቀ ሲሆን 354ቱ መዛግብት ከባለፈው ዓመት የዞሩ መሆናቸው ተጠቁሟል።
ተገልጋዮች ከመላ ሀገሪቱ ከታክስ ጋር የተያያዘ ቅሬታቸውን ለኮሚሽኑ በኦንላይን ማቅረብ እንዲችሉም ስርዓት መዘርጋቱን የጠቆሙን አቶ ሙሉጌታ ኮሚሽኑ ከመቋቋሙ አስቀድሞ የታክስ ቅሬታዎች በፍትህ ሚኒስቴር ስር ይታዩ እንደነበር ተናግረዋል።
ታክስ ጋር የተያያዙ የይግባኝ ቅሬታዎች ውሳኔ ሳያገኙ የሚዘገዩበትን አካሄድ ለማስቀረት ኮሚሽኑ ተቋቁሟል የሚሉን አቶ ሙሉጌታ በገቢዎች እና ጉምሩክ ቅርንጫፎች ባሉ የአቤቱታ አጣሪዎች ብሎም የዋና መስሪያ ቤቶቹ የቅሬታ አጣሪ ዳይሬክቶሬቶች የታዩ ጉዳዮች ላይ የሚቀርቡ የይግባኝ ጥያቄዎችን ተቀብሎ የሚያስተናግደው ኮሚሽኑ በአፈጻጸም ሂደቱ ላይ ገጠሙት ያሏቸውንም ተግዳሮቶች ተናግረዋል።
የታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ ተደራሺነቱን እና ዕውቅናውን በማስፋት የቅሬታ ምዝገባውን በኦንላይን ስርዓት በማድረግ ተገልጋዮች ለቃል ክርክር ብቻ በአካል የሚቀርቡበትን መንገድ መፍጠር ላይ እየሰራ ስለመሆኑም ተጠቁሟል።
በአብርሃም በለጠ
2022-11-08
