በዛሬዋ ዕለት ከ56 ዓመታት በፊት በአንዲት ምሽት ብቻ ሰላሳ ሚሊዮን ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የቻለ ብልሽት በሰሜን አሜሪካ አህጉር ተከስቶ ነበር። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።
ዓለም በኤለክትሪክ ብርሃን ምሽቷን ማድመቅ ብሎም በኤሌክትሪክ ኃይል እንቅስቃሴዎቿን ማድረግ ከጀመረች ሰነባብታለች። የዚሁ የኤሌክትሪክ ብርሃን መስመሮች ብልሽት ደግሞ ሚሊዮኖችን የጨለማ ምሽት እንዲያሳልፉ፣ ብዙ ስራዎች እንዲቋረጡም ያስገደዱ ሁነቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነዋል።
ጊዜው 56 ዓመታትን መለስ ስንል የምናገኘው 1958 ዓ.ም. ነው። በዚሁ ዓመት በዛሬዋ ዕለት ሚሊዮኖችን የጨለማ ምሽት እንዲያሳልፉ ያደረገ ሁነትን እናገኛለን።
ይሄው ጨለማን ለማስተናገድ የተገደደው የዓለም ክፍል ያኔም ቢሆን ባለጸጋ የሚባል መሆኑ ደግሞ ነገሩን ይበልጥ ወይ ግሩም ከተባለባቸው የኤለክትሪሲቲ ብልሽት ውጤት በሆነ በጨለማ የመዋጥ ክስተቶች አንዱ አድርጎታል።
የአሜሪካ ሰባት ግዛቶች እና ምስራቃዊ ካናዳ በዚሁ ክስተት ጨለማ ነግሶባቸዋል።ያኔም በ1950ዎቹ መጨረሻ ሰሜን አሜሪካ የኤለክትሪክ መሰረተ ልማት የተሟላለት፣ ትልልቅ ህንጻዎች የነበሩት የዓለም ክፍል ነው።
የዚህን የዓለም ክፍል የኤለክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለማሟላት የሚሰሩም ተቋማት በየስፍራው ነበሩት። የካናዳ እና አሜሪካ ድንበር ደግሞ የሃይድሮኤለክትሪክ ኃይል የሚመረትበት የአህጉሩ የኃይል ስፍራ ነው።
በዛሬዋ ዕለት በ1958 ዓ.ም. ግን ጸሐይ ከጠለቀች በኋላ አካባቢው የለመደውን የኤለክትሪክ ብርሃን እንደወትሮው የማያገኝበት ቅጽበት ተፈጠረ።
ይሄው የሰሜን ምስራቁ ታላቅ ጨለማ ተብሎ የሚጠራው ሁነት የጀመረው ብዙዎች በእንቅስቃሴ ላይ በነበሩበት መሆኑ ደግሞ ተጽዕኖውን ከፍ ያለ አድርጎታል።
የኤለክትሪክ መብራት ብልሽቱ ሲያጋጥም 800 ሺህ ሰዎች በአሜሪካ የባቡር ጣቢያዎች ነበሩ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ በቢሮ ህንጻዎች፣ በአሳንሰሮች እንዲሁም በባቡሮች ውስጥ ነበሩ።
ብዙዎች በተሽከርካሪ መንገዶች ላይ የነበሩበት ሰዓት መሆኑ ደግሞ የትራፊክ መብራቶች ከአገልግሎት ውጭ ሲሆኑ የትራፊክ መጨናነቅም ተከተለ። ክስተቱን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የብሄራዊ ዘብ ጠባቂዎች እና 5 ሺህ ፖሊሶች አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።
ይሄው በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በኤሌክትሪክ መስመር ብልሽት ከተስተናገዱ ትላልቅ የጨለማ ምሽት ሁነቶች አንዱ ክስተት ምክንያት በካናዳ ኦንታርዮ ከፍተኛ ጫና የበዛበት የ230 ኪሎ ቮልት አቅም ያለው ትራንስሚሽን መበላሸቱ ነበር። የዚሁ መስመር ላይ የደረሰው ብልሽት የሌሎች ተጓዳኝ መስመሮችን ብልሽትን አስከትሏል።
በዚሁ ሳቢያ የተፈጠረው ጨለማ በአሜሪካ ስምንት ግዛቶች እና በካናዳ የኦንታርዮ እና ቁቤክ ክፍለ ግዛቶች 30 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የኤሌክትሪክ መስመር ብልሽቱን ተከትሎ ካለው የዘጠኝ ወር ጊዜ በኋላ የወሊድ መጠን ጨምሯል የሚሉ መረጃዎችም ተስተውለዋል።
ምንም እንኳን መስል ትልልቅ የኤሌክትሪክ ብልሽት ምሽቶች ከዚያ በኋላ በቀጠናው መስተናገዳቸው ባይቀርም የቅድመ ጥንቃቄ ማሻሻያዎች እንዲደረጉም ምክንያት ሆኗል።
በአብርሃም በለጠ
2022-11-09
