አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ከምን ጊዜውም በላይ ግዙፍ የተባለ የጦር ልምምድ ማደረጋቸው ለሰሜን ኮሪያ ጥሩ ዜና አልኾነም። ጉዳዩ ለደኀንነቴ አስተማማኝ አይደለም በማለት የተለያዩ የሚሳዔል ሙከራዎች በተደጋጋሚ እያደረገች ነው።
በዕርግጥ ሀገሪቱ ከዚህ ቀደምም የሚሳዔል ማስወንጨፍ ልምምድን በተደጋጋሚ ስታደርግ ቆይታለች።የአሁኑ ግን የተለይ ይመስላል። በተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረጓ የምትጎራበታቸውን ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ነገሩ ከምን ጊዜውም በላይ አሳስቧቸዋል።
ከሕዳር 2-5 ባሉት ቀናት ውስጥ ብቻ ሰሜን ኮሪያ 80 ሚሳዓኤሎችን እንዳስወነጨፈች ነው የሲጂቲኤን ዘገባ የሚያሳየው በተጨማሪ 500 ተዋጊዎችን ያካተተ የአየር ልምምድን አድርጋለች።
ሰሜን ኮሪያ ጃፓን የአየር ክልል ላይ ሚሳዔል ማስወንጨፏ ደግሞ ነገሩ የበለጠ እንዲካረር አደርጎታል
ይህን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም ሰሜን ኮሪያን ጠንከር ባለ ቃላት አስጠንቅቀዋል።
ሀገሪቱ በቅርቡ የባለስቲክ ሚሳዓኤል ማስወንጨፏን ተከትሎ እያደረግሽ ካለው ጸብ አጫሪ ድርጊት በአስቸኳይ ታቀቢ ሲሉ ጸሓፊው አሳስበዋል።
ይህን ተከትሎ ሰሜንኮሪያ የተመድን ማሳሰቢያ ተገቢ ያልኾነ እና ጭፍን ፍረጃ ነው ስትል አውግዛለች።
የሰሜን ኮሪያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ባደረጉት ንግግር በኮሪያ ልሳነ ምድር እየተባባሰ ለመጣው ውጥረት ተመድ አንዱ ተወቃሽ የሚኾን ይመስለኛል ብለዋል። ድርጅቱ እንዲሁ ዝም ብሎ ነገሮችን ሳያመዛዝን በጭፍን ነው ወቀሳውን ያቀረበው ብለዋል።
እኛ ከአሜሪካ ሊቃጣብን የሚችለውን የደኀንነት ስጋት ለመመከት የሚያስችል ልምምድ ነው እያደረግን ያለነው ብላለች ሰሜን ኮሪያ ስለሚሳዔል ማስወንጨፍ ሙከራዋ ስትናገር።
ሌላው ፒዮንግያንግ ከሩሲያ ጋር የጦር መሳሪያ ለመገበያየት ስምምነት አድርጋለች የሚል ነበር። ይህንንም ወቀሳ አጣጥላለች እንዲህ ዓይነት ስምምነት ኾነ ዕቅድ ከሩሲያ ጋር ኖሮኝ አያውቅም ወደፊትም አይኖረኝም ስትል አስታውቃለች።
ከዓለም የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተገለለችው ሰሜን ኮርያ የኒኩለር ባለቤ መሆኗና አሁን በጎረቤቶቿ ላይ እየፈጠረችው ያለው ሥጋት መናር አካባቢውን ወደ ጦርነት ቀጠናነት እንዳትለውጠው አስግቷል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-11-09
