ሀገሬ ቲቪ

በሰሜን ኮሪያ ላይ የታሰበው ማዕቀብ

ሰሜን ኮሪያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል አሜሪካ ጉትጎታዋን አጠናክራለች ተባለ፡፡ ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራዎችን ስታደርግ የቆየች ሲሆን ፤ ይህ ድርጊቷ ሲያስወቅሳት እና ሲያስወግዛት ቆይቷል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔን በመጣስ ተከታታይ የሚሳኤል ሙከራ ባደረግቸው ሰሜን ኮሪያ ትዕግስቴ ተሟጧል ብላለች ፡፡ አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሀገሪቱ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጥል እየወተወተች መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በቲውተር ገጻቸው የአሜሪካንን አቋም አስፍረዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ የሚደርስባትን ዛቻ እና ማስፈራራያ ከቁብ ሳትቆጥር ካለፈው ከፈረንጆቹ ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ስድስት የሚሳአል ሙከራን አድርጋለች፡፡ ከሚሳኤል ሙከራው በኋላ አሜሪካ ተጨማሪ ማዕቀብ ካልጣልንባት ከድርጊቷ ልትቆጠብ አትችልምና ማዕቀብ ይጣል ስትል ከርማለች፡፡ ሰሜን ኮሪያ ማክሰኞ ዕለት ነበር ሀይፐር ሶኒክ የተባለ እና ፍጥነቱ ከድምጽ ፍጥነት የላቀ ነው የተባለ ሚሳኤል መሞከሯን ያስታወቀችው፡፡

በሀገሬ ቲቪ
2022-01-13