ዓለማችን ታላቁ ጦርነት ስትል ስያሜ የሰጠችው፤ ከ16 ሚሊዮን የሚልቁ ወቶአደሮች እና ሲቪሎችን የቀጠፈው፤ 21 ሚሊዮኑን አካል ያጎደለው ያ ላቁ ቅዠት ከዛሬ 104 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ዕለት መቋጫውን አደረገ።
ነገሩ 4 ዓመታን ይቀድማል፤ ሐምሌ 11 1906 ዓ.ም. የአውስትሮ-ሃንጋሪ ግዛት አልጋ ወራሽ አርክዱክ ፍራንዝ ፈርዲናንድ በቦስኒያ ሰርብ ጋቭሪሎ ፕሪንሲፕ በሳራዬቮ፣ ቦስኒያ ከባለቤቱ ጋር ሳለ በጥይት ተመትቶ ተገደለ።
ኦስትሪያ-ሃንጋሪ ለጥቃቱ የሰርቢያን መንግስት ተጠያቂ አደረገች። ሩሲያ ከሰርቢያ ጎን ተሰለፈች ሌሎቹም የአውሮፓ ሀገራት ጎራቸውን ለዩ።
ሐምሌ 22 ቀን የኦስትሮ-ሃንጋሪ ሃይሎች የሰርቢያን ዋና ከተማ ቤልግሬድን በጦር መሳሪያ መደብደብ ጀመሩ። የተፈራው ቅዠት፤ ታላቁ የዓለም ጦርነት 1 ብሎ ጀመረ።
ሩሲያ፣ ፈረንሳይ፣ ፈረንሣይ እና ታላቋ ብሪታንያ ጦርነቱን ወዲያውኑ ተቀላቀሉ። የሰርቢያ ወዳጅ የሆነችው ሩሲያ በኦስትሪያ-ሃንጋሪ ላይ ወታደራዊ ዘመቻን ለማድረግ ትቀሰቅስ ገባች። ከሪሲያ ጎን ነኝ ያለችው ፈረንሳይም ጦሯን ማሰባሰብ ጀመረች።
ሐምሌ 27 ጀርመን እና ፈረንሳይ ጦርነት አወጁ። ጀርመን በርካታ ኪሎሜትሮችን አቋርጣ ቤልጀምን ወረረች።
የቤልጄም መወረር ያስቆጣት የዛኔዋ ታላቋ ብሪታኒያ በጀርመን ላይ ጦርነትን አወጃ ትልቁን ጦርነት ተቀላቀለች። አንደፈርም ያሉ አውሮፓውያን በሁለቱም ጎራ ጦርነቱን ተቀላቀሉ።
በቶልፕ ይጠናቀቃል የተባለው ጦርነት ቀናትን እየወለደ ቢሻገርም ከድል ይልቅ ሌላ ጦርነትን እየወለደ ተሻገረ።
ሴንትራል ፓወር ወገን - ጀርመን፣ ኦስትሪያ-ሃንጋሪ፣ ቡልጋሪያ እና የኦቶማን ኢምፓየር (ቱርክ) ሲሰለፉ፤ አሊያንስ ወገን - ታላቋ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ኢጣሊያ፣ ሮማኒያ፣ ካናዳ፣ ጃፓን እና ከ 1910 ዓ.ም. በኋላ አሜሪካ ተቀላቅላ ተዋግተዋል።
በግዜው የነበረው የጦር መሳሪያ ፈጠራ በሌሎች ጦርነቶች ላይ ታይቶ የማይታወቅ የሰው እልቂት እንዲፈጠር አድርጓል።
በ1907 ዓ.ም. አጋማሽ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ወታደሮች በአውሮፓ የጦር አውድማዎች ላይ ረገፉ።
በጦርነቱ ንፁሃን ሳይቆጠሩ ዘጠኝ ሚሊዮን ወታደሮች ሲሞት 21 ሚሊዮን የሚሆኑት አካላቸውን አጥተዋል። ጀርመን፣ ሩሲያ፣ ኦስትሪያ-ሃንጋሪ፣ ፈረንሣይ እና ታላቋ ብሪታንያ እያንዳንዳቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎቻቸውን አጥተዋል።
ቢያንስ 5 ሚሊዮን ንፁሀን ዜጎች በበሽታ፣ በርሃብ እንዲሁም ለጦርነቱ በመጋለታቸው ሳቢያ ሞተዋል። ከ16 ሚሊዮን የሚልቅ ነፍስ በሜዳ ቀርተዋል።
ሐምሌ 11 1906 ዓ.ም. እንደዋዛ የጀመረው ጦርነት ኅዳር 2 1911 ዓ.ም. ቀን ጀርመን ከአሊያንሶቹ ጋር ለስምምነት ተቀመጠች።
ለታሪካዊው ስምምነት የናፖሊዮን ሦስተኛ ባቡር ተመረጠች በዚያች ባቡር ፉርጎ ውስጥ ተቀምጠው አንዳች የተኩስ ድምጽ ላለማሰማት ተማማሉ።
በዚያም የጦርነቱ ማብቃት ታወጀ። ይህ የዛሬ 104 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ሆነ።
በሳምሶን ገድሉ
2022-11-11
