ባቡር የትራንስፖርት ዘርፉ ወደ ዝማኔ ሲምዘገዘግ አብሮ የተገኘ፣ ከዘመን ዘመን እየተሻሻለ የመጣ የቴክኖሎጂ ውጤት ነው።
ከአውሮፓ ሃገራት አንዷ የሆነችው ስዊዘርላንድ ደግሞ ከሰሞኑ የመጀመሪያ ባቡሯን 175ተኛ ዓመት ስታከብር የዓለማችንን ረዥሙን ባቡር እንካችሁ ብላ ከዓለም የረዥሙ ባቡር ባለቤት በመሆን በቀዳሚነት ስሟ እንዲመዘገብ አድርጋለች።
ይሄው በርዝመቱ ዓለምን ያስደመመው የስዊስ ባቡር የ1 ሺህ 900 ሜትሮች ርዝመት ያለው ነው።
ባቡሩ በስዊስ ተራራዎች ላይ ተንሸራሽሮባቸዋል። ምንም እንኳን የስዊዘርላንድ ተራራማ የባቡር መስመሮች እምብዛም ለጉዞ ምቹ ናቸው ባይባልላቸውም ወደ ሁለት ኪ.ሜ. የሚጠጋው ርዝመት ያለውን የዓለማችንን ረዥም ባቡር ከማስተናገድ አላገዳቸውም።
ይሄው ረዥሙ ባቡር በተራራማ መስመሮቹ ላይ መምዘግዘጉ ደግሞ ይበልጥ እይታውን ማራኪ አድርጎታል ተብሎለታል።
ባቡሩን ለማንቀሳቀስ ደግሞ የባቡሩ ቴክኒሻኖች ከፍተኛ መናበብ ይጠበቅባቸው ነበር። የፍጥነት ተመሳሳይነት ወሳኝ ድርሻ ነበረው።
ለ175ተኛው የስዊዘርላንድ የመጀመሪያው ባቡር ክብረ በዓል የ25 ኪ.ሜ. ጉዞውን ያደረገው ባቡሩ የ11 ሺህ ቮልት አቅም ያለው ኃይል ዝግጁ ሆኖለትም የአካባቢውን የኃይል አቅርቦት ያዛባው ይሆን የሚል ስጋትን አሳድሮም ነበር።
ለስጋቱ ምክንያት ደግሞ የ25 ባቡሮች ድምር የሆነው ይሄው ባቡር በተመሳሳይ ጊዜ በተመሳሳይ የባቡር ሃዲድ ላይ 25 ባቡሮች ቢጓዙ ሊጠቀሙ የሚችሉት ኃይል የአካባቢውን የኃይል አቅርቦት ያዛባል የሚል ነበር።
3000 ሺህ የሚደርሱ ዕድለኛ ተሳፋሪዎች በታሪካዊው የ1.9 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ባቡር የተራሮች ላይ ጉዞን ታድመዋል። የተጓዦችን ደህንነት ለመጠበቅ የደህንንነት መጠበቂያ መንገዶች ቢዘጋጁም ጉዞው በስኬት ተጠናቋል።
የባቡሩ ታሪካዊ ጉዞ በ19 ካሜራዎች፣ በአውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች ጭምር እንዲቀረጽ ተደርጎ ለዓለም እንካችሁ ተብሏል ሲል የዘገበው ኦዲቲ ሴንትራል ነው።
በአብርሃም በለጠ
2022-11-11
