በአማራ ክልል፤ በሰሜን ሸዋ ዞን የምትገኘው የአጣዬ ከተማ ከ 2010 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ባሉት አራት ዓመታት ተደጋጋሚ ግጭቶችን አስተናግዳለች።
በእነዚህ ግጭቶች ምክንያት 423 መኖሪያ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸው የሚታወስ ነው። አሁን ላይ የከተማዋ አስተዳደር ከመንግሥት እና ከተለያዩ ድጋፍ አድራጊ ተቋማት ባገኘው ዕርዳት መኖሪያ ቤቶችን መልሶ የመገንባት ሥራ ጀምሯል።
ይሁን እንጂ እስካሁን 80 ቤቶችን ብቻ መገንባት እንደቻለ የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አቶ አሳልፍ ደርቤ ለሀገሬ ቴቪ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት በሰጠው 24 ሚሊዮን ብር 45 ቤቶች ተገንብተዋል። ካናዳ የሚኖሩ ዜጎች እና ሌሎች ተቋማት ባደረጉት ድጋፍ በተመሳሳይ 45 ቤቶች መገንባታቸውን ነው አቶ አሳልፍ የተናገሩት።
52 ሺህ የሚጠጋ ተፈናቃይ ዜጋ በከተማዋ ውስጥ እንደነበር እና 80 በመቶ የሚኾነውን ተፈናቃይ ወደ ቀድሞ አካባቢው እንዲመለስ ማድረግ እንደተቻለ ከንቲባው ገልጸዋል።
አኹንም ቢኾን ቤትንብረታቸው የወደመባቸው እና መልሰው መሥራት ያልቻሉ ዜጎች በተፈናቃይ መጠለያዎች ይገኛሉ። ገሚሶቹ ደግሞ ወደ አጎራባች ወረዳዎች መሰደድ ግድ ኾኖባቸዋል።
በደረሰው ጉዳት ልክ የማቋቋም ሥራው እየተሰራ እንዳልኾነ አቶ አሳልፍ ደርቤ ገልጸዋል። መንግሥትም ኾነ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
በአጣዬ ከተማ ከ 2010 ጀምሮ በነበሪት ግጭቶች በአጠቃላይከ225 በላይ ንጽኃን ሞተዋል፤3.2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ደግሞ ወድሟል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-11-14
