ለሚቀርቡ የክልልነት ጥያቄዎች ለእያንዳንዳቸው የተናጠል የክልልነት ምላሽ መስጠት ተመራጭ እንደማይሆን ተገለጸ። ማህበረሰቡ ባለበት ክልል ፍትሐዊ የሃብት ተጠቃሚ እንዲሆን ፣ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ብሎም መልካም አስተዳደር እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል።
በፌደሬሽን ምክር ቤት የተመዘገቡ 56 ብሄረሰቦችን ያቀፈው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአደረጃጀት ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ የክልል እንሁን ጥያቄዎችን በማስተናገድ ላይ ነው።
ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው የፌደራሊዝም እና ህገ መንግስት አስተምህሮ ማዕከል ዋና ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኃ/ኢየሱስ ታዬ ማህበረሰቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች ተቀብሎ ተገቢ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ብለውናል።
ሊተኮርበት የሚገባው ዋና ጉዳይ ግን የክልልነት ምላሽ መስጠቱ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡ እኩል ተጠቃሚነት እና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖረው ማድረጉ ላይ ነው ባይም ናቸው።
ደቡብ ክልል ከሌሎች የሀገራችን ክልሎች በይበልጥ ብዙ ብሄረሰቦችን ያቀፈ መሆኑ አሁን ላይ ተደጋጋሚ የክልልነትን ጥያቄዎችን እንዲያስተናግድ አድርጎታል ያሉን የፌደራሊዝም እና ህገመንግስት አስተምህሮ ማዕከል ዋና አሰልጣኝ አቶ ዘውዴ ደምሴ ለእያንዳንዱ የክልልነት ጥያቄ የተናጠል ክልልነት ምላሽ መስጠት ከባድ ስለሚሆን በክላስተር ወይም ህብረ ብሄራዊ መልክ ማደራጀቱ የተሻለ ነው ብለዋል።
ህገመንግስቱ በፌደሬሽን ምክር ቤት እውቅና ለተሰጣቸው ብሄረሰቦች ክልል የመሆን ጥያቄ የማቅረብ ነጻነትን ቢሰጥም ለሁሉም የክልልነት ጥያቄዎች ግን የተናጠል አወንታዊ ምላሽ መስጠት የሚቻል አይሆንም የሚሉት ዶ/ር ኃ/ኢየሱስ ታዬ ዋናው መፍትሄ ማህበረሰቡ በየተደራጀበት ክልል መልካም አስተዳደርን በመፍጠር ባለቤትነት እንዲሰማው ማድረግ ነው ብለውናል።
በአብርሃም በለጠ
2022-11-14
