የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና የቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ሊገናኙ ነው። መሪዎቹ ታይዋንን ጨምሮ ሀገራቱ በገቡባቸው ውጥረቶች ላይ ይመክራሉ ተብሎም ይጠበቃል።
በነሐሴ ወር በ2003 ዓ.ም. ሲገናኙ ሁለቱም ለሀገራቸው ምክትል ፕሬዚዳንቶችነበሩ። የአሜሪካው ጆሴፍ ሮቢኔት ባይደን እና የቻይናው አቻቸው ሺ ጂንፒንግ።
ያኔ ነገሮች እንደዛሬው አልነበሩም፤ በትልቁ ቤተ-መንግስት ተጨባብጠው፤ ለሰዓታትም መክረው ነበረ ፤ ባይደን እንዲህ ብለውም ነበር።
‘’ሁለቱ የዓላማችን ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገራት የዓለም ኢኮኖሚ እንዲያገግም መንገድ እንደሚሆኑ በጣም እተማመናለው። ረዘም ያሉ ሰዓታትን ተወያይተናል፤ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ባሉት ነገር እስማማለው ውድድር ጤናማ ነው።በጣም ጥሩ ነው፣ ያነቃናል፣ በድጋሚ እንድንበረታ ያደርገናል።ቻይና በአሜሪካ የምታደርገውን ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በበጎ እንቀበለዋለን።‘’
ከ11 ዓመታት በኋላ ለሀገራቸው መሪ ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ በአካል ሊገናኙ መሆኑ ተሰምቷል። ሁለቱ ሀገራት አሁን ከቀድሞ በባሰ ሁኔታውስጥ እንዳሉ በርካቶች ይስማሙበታል።
ንግድ፣ የታይዋን ፖሊሲ፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበርም ቢሆን አሜሪካ ከግዜ ወደ ግዜ ለቻይና ጀርባዬን እንድሰጥ ያደረጉኝ ጉዳዮች ናቸው ባይ ናት።
መሪዎቹ በህዳር 2014 ዓ.ም. በቪዲዮ ኮንፍረንስ ለመምከር ቢሞክሩም፤ ነገሩ ግን ከውይይት ይልቅ እርስ በዕርስ ማስፈራሪያ እና ዛቻን የተለዋወጡበት ይመስል ነበር። ለዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት እየባሰ መምጣቱ ማሳያ ነው ባዮች በርካታ ናቸው።
አሁን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ሆነ ዢን ፒንግ ኢንዶኔዢያ ደርሰዋል። በዚያ የቡድን 20 ዓባል ሀገራት ስብሰባ አለባቸው።
ታዲያ በኢዶኔዢያዋ ባሊ በሚኖራቸው ቆይታ፤ ሀገራቱ ስለገቡበት ውጥረት፣ ስለ ዓለም ኢኮኖሚ በጥልቀት ይመክራሉ ተብሊም ይጠበቃል።
በተለይ በተለይ አሜሪካን እንቅልፍ የነሳት የኒውክለር የጦር መሳሪያ ጉዳይ፤ ባይደን ሺን አብዝተው እንዲፈልጉ ያደረጋቸው ምክንያት እንደሆነ የምዕራባውያን መገናኛ በዙኃን እየዘገቡ ይገኛሉ።
ከታይዋን እስከ ሩሲያ ከፍ ሲልም ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካ ራስምታት መነሻዎችም መድረሻዎችም ናቸው። ለዚህም ይመስላል ባይደን አብዝተው ቀይ መስመሮቻችንን መለየት አለብን ማለታቸው።
“ቀይ መስመሮቻችን የቱ ጋር ናቸው የሚለውን መለየት ይኖርብናል። ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የምናልፍበት ለሁለታችንም በጣም አንገባጊዎቹ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው እሚለውን መለየት ይኖርብናል።”
ባይደን ታይዋን በአሜሪካ ወዳጅነት ላይ እንድትተማመን ይሻሉ፤ የመገናኘታቸው ፍሬ ነገርም ይህ ነው ይላሉ የባይደን የደህንነት አማካሪያቸው ጃክ ሳሊቫን።
“እንደ አስተዳደር ስለ ስብሰባው ውጤት ለታይዋን ማብራሪያ እንሰጣለን። ታይዋን በአሜሪካ አጋርነት እና አቋም ላይ መተማመን እንደምትችል አምናለው። ከታይዋን ጋር ያለን ኝኙነት በታይዋን ጎዳናዎች ሰላም እንዲመጣ ለታይዋን መከላከያ እገዛ እስከ ማድረግ የሚደርስ ነው።”
ታዲያ ለዚሁ የአሜሪካ ፍላጎት ቻይና ዝምታን አልመረጠችም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩአ በኩል ምላሽ ሰትታለች።
የታይዋን ጉዳይ የቻይና የውጪ ፖሊሲ መሰረት ነው። አሜሪካ ይህንን የሚፃረረው ተግባሯን ማቆም ይኖርባታል።
ባይደን ከቻይናው አቻቸው ጋር ከመቀመጣቸው አስቀድመው፤ የቻይናን ጉልበት ሚዛን ያስጠብቁልኛል ኪሚሏቸው አጋሮቻቸው ጃፓ እና ደቡብ ኮሪያ መሪውች ጋር ተገናኝተውም ነበር።
በዚያ ሆነውም ሰሜን ኮሪያ እያደረገች ነው ያሉትን የሚሳኤል ሙከራ፤ የፀብ ጫሪነት ድርጊት ለመቋቋም ህብረቱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬንም የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ሌላኛው ጉዳያቸው ነው።
ቻይና ዩክሬን ጉዳይ የያዘችው አቋም አሜሪካን ያስከፋ እንደሆነም ይታወቃል፤ የባይደን የደህንነት አማካሪያቸው ጃክ ሳሊቫን የባይደንን ከቻይናው አቻቸው ጋር መገናኘት ወሬ ባቀበሉበት መግለጫቸው፤ ሁለቱ መሪዎች መገናኘታቸው የተሻለ ግንኙነት እንዲኖር እና ልዩነቶቻቸው ላይ መግባባት ለመፍጠር እና ልዩነቶቻቸውን ለማወቅ መሆኑን ተናግረው ነበር።
ከወራቶች በፊት የአፈጉባኤዋ ናንሲ ፔሉሲ የታይዋን ጉብኝት ያጎረበጠው፤ ቀድሞም በሩሲያ ጉዳይ ቂም ያቋጠረው የቻይና እና የአሜሪካ ግንኙነት በመሪዎቹ መገናኘት የሚለሳለስ ይሆን። ግዜ ቀጣዩን መልስ ያቀብለን ይሆናል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-11-14
