አጼ ቴውድሮስ በመቅደላ ጦርነት ሲወድቁ በእንግሊዝ ወታደሮች የተማረከው ልዑል ዓለማየሁ በእንግሊዝ 12 አመታትን ከኖረ በኋላ በዛሬው ቀን ከ 143 አመት በፊት ነበር ከዚህ አለም በሞት የተለየው። የዕለቱን ከታሪክ ትኩረታችን ነው።
የዓፄ ቴዎድሮስ ወንድ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ መወለድ በንጉሱ ቤት ደስታን የፈጠረ ነበር።
አጼ ተውድሮስ በልዑሉ መወለድም ደስ ተሰኝተው ፟መድፍ እንዲተኮስ እና ከ 500 በላይ እስረኞች እንዲለቀቁም አደርገዋል ። ለልጃቸው ልዩ ፍቅር የነበራቸው አጼ ቴውድሮስ ብዙን ጊዚያቸውን ከ ልጃቸው ጋር በጫወታ ያሳለፉ ነበር።
ዐፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ ሲወድቁ ከሁለተኛ ባለቤታቸው እቴጌ ጥሩወርቅ የሚወለደው ልዑል አለማየሁ ያን ግዜ እድሜው ስምንት ብቻ ነበር፡፡ ከ ንጉስ አጼ ቴውድሮስ ሞት በኋላ ጄኔራል ሜርዌዘር ወደ እንግሊዝ በላከው ወታደራዊ የሚስጥር መልዕክት "የዘውዱን ወራሽ አግኝቼዋለሁ አለ"፡፡
ልዑል አለማየሁም ከእናቱ እቴጌ ጥሩወርቅ ጋር በእንግሊዞች እጅ ወደቀ፡፡ ጄኔራል ናፒር ከእቴጌ ጥሩወርቅ ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት አጼ ቴውድሮስን በቅርበት ያውቃቸው ለነበረው እና አማርኛን አቀላጥፎ ለሚናገረው ካፒቴን ጄ.ሲ. ስፒዲ ተሰጠ፡፡
ናፒር ልዑል አለማየሁ ከእናቱ እቴጌ ጥሩወርቅ፤ ከመምህሩ አለቃ ዛራት የእናቱ አጃቢ ገብረመድህን ጋር ሆኖ ከሃገሩ እንዲወጣ አደረጉ፡፡ በመንገድ ላይ እያሉ እናቱ እቴጌ ጥሩወርቅ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡
በመጨረሻዋ የህይወታቸው ቅፅበት ግን ስፒዲ ልዑል አለማየሁን እንደ አባት ሆኖ እንዲያሳድገው ቃል አስገቡት፡፡ በፋሪዝ በትባለችው መርከብ የተሳፈሩት ልኡል አለማየሁ የአደራ አሳዳጊው ከነበርው ስፒዲ ጋ እንግሊዝ ደረሱ ።
በአጭር ጊዜ አባቱን እና እናቱን በሞት የተነጠቀው ልኡሉ ከፍተኛ ሃዘን ወስጥ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንድም የሚያውቀው ሰው በአጠገቡ ያልነበረው ልዑል አለማየሁ ከስፒዲ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሰረተ፡፡
ንግስት ቪክቶሪያ የልዑል አለማየሁን መያዝ ከሰማች ጀምሮ እንደ እናት እንክብካቤ እዲደረግለት ትዕዛዝ ሰጥታ ነበር፡፡ ንግስት ቪክቶሪያ ኢትዮጵያዊውን ልዑል እጅግ ወዳው ስለነበር በተደጋጋሚ ወደ ቤተመንግስት ታስጠራው ነበር፡፡
በግል ማስታወሻዋ ልዑሉን ማየት የፈጠረላትን ስሜት እንዲህ በማለት ጸፋለች ፡፡ከምሳ በሃላ ወደ እኔ ሳሰጠራው የሚያምረውን የአቢሲኒያ ልብሱን ለብሶ ነበር የሚመመጣው እኔም የእጅ ሰአት ስጦታን በእጁ አስሬለት ነበር ።
አሳዳጊው ካፒቴን ስፒዲ በህንድ ጦር ሰራዊት በሚያገለግልበት ወቅት ልዑል አለማየሁ አብሮት ተጉዞ ነበር ፡፡ ባይተዋሩ ልዑል በእንግሊዝ እንክብካቤ ቢበዛለትም ሙሉ ህይወቱን ደስተኛ ሆኖ የኖረ አይመስልም ምክያቱ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ከንግስቷ በመጡ ትዕዛዞች የመኖሪያ አካባቢው ይቀያየር ሰለነበር፡፡
የቀለም ትምህርት የጀመረው ልኡል የሚያስተምሩት መምህራን ወታደራዊ ሳይንስ እንዲያጠናም ግፊት አድርገወበት ሳንድረስት ወታደራዊ ትምህርት ቤት ካለ ፈተና እንዲገባ ተደረገ፡፡በወታደራዊ ትምህርት ቤት ደስተኛም ሆነ ውጤታማ ያልንበረው ልኡሉ ለእረፍት እንደወጣ አልተመለሰም፡፡
ልኡል አለማየሁ ከኢትዮጵያ ሁለት ደብዳቤዎች ደርሰውት ነበር፡፡ አንዱ ከእናቱ እናት ወይም ከአያቱ ሲሆን የሁለተኛው ደብዳቤ ላኪ ማንነት አይታወቅም፡፡ ሁለቱም ደብዳቤዎች የልኡሉን መመለስ በአጅጉ የሚናፍቁ ነበሩ፡፡
በእንግሊዝ ስደተኛ እና ባይተዋር የነበረው ልኡል አለምአየሁ ከዛሬ 143 አመት በሳንባ ምች በሽታ ታሞ በዛሬው ቀን በ 19 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ ፡፡ የቀብር ስነ ስረአቱም በንግስቷ ፈቃድ በዊንድሶር የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተመቅደስ ተፈፀመ፡፡
በወንድምአገኝ አበበ
2022-11-14
